ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ በዚህ ዓመት እስከ ዘጠኝ በመቶ እንደምታድግ ተገምቷል

አዲስ አበባ ጥር 24/2011 በተያዘው ዓመት የኢትዮጵያ አጠቃላይ ዕድገት እስከ ዘጠኝ በመቶ ሊሆን እንደሚችል የዓለም ባንክ መተንበዩን ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ገለፁ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከህዝብ ተወካዮች ምክር አባላት ለተነሱ ጥያቄዎች ማብራሪያና ምላሽ ሰጥተዋል።

በማብራሪያቸው እንዳሉት የዓለም ባንክ የኢትዮጵያን የበጀት ጉድለት ለመሙላት የ1 ነጥብ 7 ቢሊዮን ዶላር ብድርና እርዳታ ሰጥቷል።

ባንኩ ለኢትዮጵያ እንዲህ አይነት ከፍ ያለ ድጋፍ ሲያደርግ በታሪኩ የመጀመሪያ መሆኑንም አስረድተዋል።

በአገሪቱ ባለፉት 15 ዓመታት በአማካይ 14 በመቶ የነበረውን የዋጋ ግሽበት አሁን 10 ነጥብ 3 በመቶ ማድረስ ተችሏል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህ የሆነው የመንግስትን ወጪ መቀነስ በመቻሉ ነው ብለዋል።

አሁን መንግስት ትኩረት ያደረገውም የተጀመሩ ግዙፍ የፕሮጀክት ግንባታዎች ላይ መሆኑን ተናግረዋል።

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ በ80 ቢሊዮን ብር ተጀምሮ አሁን 60 በመቶ ጭማሪ ማሳየቱን አስታውሰዋል።

በመሆኑም ግንባታው በቀጣይ ተጨማሪ ወጪ እንዳያስከትል ግንባታውን በአራት ዓመታት ሙሉ ለሙሉ ለማጠናቀቅ እየተሰራ መሆኑን ለምክር ቤቱ አባላት አስረድተዋል።

በአገሪቱ በኢንቨስትመንት ዘርፍ የነበረውን ማነቆ በመፍታት አዳዲስ የውጭ ባለሃብቶች ወደ አገር ውስጥ እየገቡ መሆኑንም ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ የገለጹት።

በዚህ ዓመትም የውጭ ባለሃብቶች በቢሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ይዘው ስራ ለመጀመር ወደ ኢትዮጵያ መግባታቸውን አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም