መከላከያ ሰራዊቱ ባለፉት 100 ቀናት ኢትዮጵያ ውስጥ ምርጥ ስራ ከሰሩ ተቋማት መካከል አንዱ ነው-ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ - ኢዜአ አማርኛ
መከላከያ ሰራዊቱ ባለፉት 100 ቀናት ኢትዮጵያ ውስጥ ምርጥ ስራ ከሰሩ ተቋማት መካከል አንዱ ነው-ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ
አዲስ አበባ ጥር 24/2011 የአገር መከላከያ ሰራዊት ባለፉት 100 ቀናት ኢትዮጵያ ውስጥ ምርጥ ስራ ከሰሩ ተቋማት መካከል ዋነኛው እንደሆነ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለቀረበላቸው ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ እየሰጡ ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት፤ ባለፉት አመታት ኢትዮጵያን ከልዕልናዋ ለማውረድና ለመድፈር ተሞክሮ የመከላከያ ሰራዊቱ ሰንፎ ያሳለፈበት ጊዜ የለም።
ባለፉት ወራት ክልሎች ሰላምን ለማረጋገጥ በሰው ሰራሽና በተፈጥሮ ምክንያት ችግሮች ሲገጥሟቸው ሰራዊቱ ገብቶ መስዋእትነት በመክፈል ማረጋጋት መቻሉንም አስታውሰዋል።
''ሰራዊቱ በተዋጽኦ፣ በአደረጃጀት፣ በአሰራርና በሌሎችም ተግባራት ባለፉት ጊዜያት ኢትዮጵያ ውስጥ ምርጥ ስራ ከሰሩ ተቋማት መካከል ዋነኛው ነው'' ሲሉ ተናግረዋል።
መከላከያ ሰራዊቱ በአሁኑ ወቅትም በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ አገር ለሚሰጠው ሃላፊነት ህይወቱን እየገበረ የአገሪቱን ሰላም ለማረጋገጥ እየሰራ እንደሚገኝም አጽንኦት ሰጥተዋል።
ክልሎች በየአካባቢያቸው ለሚከሰቱ ችግሮች ከህዝባቸው፣ ከአገር መከላከያና ከፌደራል መንግስት ጋር በመሆን ሰላምን ማረጋገጥ እንዳለባቸው አመልክተዋል።
ለዚህም ክልሎች ራሳቸውን አጠናክረው ሰላማቸውን ማረጋገጥ እንዲችሉም መንግስት ድጎማ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል።