ቀጥታ፡

"ያለ ሚዲያ ጠንካራ ተሳትፎ የዘላቂ ሰላም ስራ አይታሰብም" - ወይዘሮ ሙፈሪሃት ካሚል

አዲስ አበባ ጥር 23/2011 "ያለ ሚዲያ ጠንካራ ተሳትፎ የዘላቂ ሰላም ስራ አይታሰብም" ሲሉ የሰላም ሚኒስትሯ ወይዘሮ ሙፈሪሃት ካሚል ተናገሩ።

የኢትዮጵያ ሚዲያ ካውንስል፣ የኢትዮጵያ ብሮድካስት ዘርፍ ማህበር እና የሰላም ሚኒስቴር በጋራ በመሆን የሰላም ሚዲያ ህብረት ትስሰር ለመፍጠር የሚያስችል ውይይት ዛሬ ማምሻውን አካሂደዋል።

ሚኒስትሯ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፣ የሰላም ሚኒስትር የተሰጠውን ተልእኮ ከሚዲያ ተሳትፎ ውጪ ማሳካት አይቻልም። 

በኢትዮጵያ ዘላቂ የሆነ ሰላምን ለመገንባት የሚደረገው ጥረት በሚዲያ ካልታገዘ ውጤት ሊያመጣ እንደማይችል ነው በውይይቱ ላይ የተነገረው።

በመሆኑም ሚዲያው ነጻነቱንና ሙያዊ ስነ-ምግባሩን በመጠበቅ ሰላምን ለማረጋገጥ እንዲሰራ ሚኒስትሯ ጠይቀዋል።

ያለንን አገራዊ እሴት በማስፋት ሰላምን ለማረጋገጥ መስራት ያስፈልጋል ሲሉም አመልክተዋል።

ሚዲያው በሰላምም ሆነ በሌሎች ጉዳዮች ተከታይ ሳይሆን አጀንዳዎችን ቀርጾ በቀዳሚነት መስራት እንዳለበት ነው ያስገነዘቡት።

የሚዲያ ተፈጥሯዊ ባህሪ ሰላም መሆን እንዳለበት ያሳሰቡት ሚኒሰትሯ የመገናኛ ብዙሃን የግጭት ጉዳዮችን ሲዘግቡ ግጭቱን በሚያባብስ መንገድ ሳይሆን ማርገብ ብሎም ማስወገድ በሚቻልበት ስልት ላይ መስራት እንዳለበት ተናግረዋል።

ሰላምን ከመስበክ ጎን ግጭት የሚያስከትሉ ጉዳዮች እንዲፈቱ የቅድመ መከላከል የሚዲያ ተግባርም ማከናወን እንደሚጠበቅ ጠቁመዋል።

በመድረኩ ተሳታፊ የነበሩት የተለያዩ የሚዲያ ሃላፊዎች በሰላም ዙሪያ በጋራ መስራት ያስፈልጋል የሚል አስተያየት ሰጥተዋል።

ከሪፖርተር ጋዜጣ የመጡት አቶ አማረ አረጋዊ ሰላምን ለመፍጠር የሚዲያ ግዴታ በመሆኑ ስነ-ምግባርን ጠብቆ መስራት እንደሚገባ  ተናግረዋል።

በጥምረት መስራት ይቻል ዘንድም ልዩነት የሚፈጥሩ አሰራርና አካሄዶችን ማስወገድና የጋራ መግባባት እንደሚያስፈልግም አሳስበዋል።

ሌላኛው የመድረኩ ተሳታፊ ሱራፌል ወንድሙ ሰላምን ለማረጋገጥ ዘላቂ መፍትሄዎች ላይ ማሰብ እንደሚያስፈልግ ገልጸው የሴቶች፣ የአካል ጉዳተኞችና ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎችን በብቃት ማሳተፍ የሰላም ጉዳይ ተደርጎ መወሰድ አለበት ብለዋል።

ከዚሁ ቀደም በልማት ጋዜጠኝነት ስም ይሰሩ የነበሩ ስራዎች አሁን ለሚታዩ አንዳንድ ችግሮች ምክንያት እንደሆኑ አስታውሰው የሰላም ጋዜጠኝነትም ከዛ ጋር እንዳይገናኝ ለማድረግ ተገቢ ጥንቃቄ መወሰድ እንዳለበትም አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም