በሊጉ 14ኛ ሳምንት ጨዋታ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከፋሲል ከነማ የሚያደርጉት ጨዋታ ይጠበቃል - ኢዜአ አማርኛ
በሊጉ 14ኛ ሳምንት ጨዋታ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከፋሲል ከነማ የሚያደርጉት ጨዋታ ይጠበቃል
አዲስ አበባ ጥር 23/2011 በ14ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከፋሲል ከነማ የሚያደርጉት ጨዋታ ይጠበቃል።
የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 14ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ቅዳሜ እና እሁድ በአዲስ አበባ እና በክልል ስታዲየሞች ይካሄዳሉ።
በሳምንቱ ማብቂያ ጅማ አባጅፋር ከባህርዳር፣ አዳማ ከወላይታ ዲቻ፣ ስሁል ሽረ ከወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ፣ ሲዳማ ከደደቢት፣ መቐለ አብአ እንደርታ ከመከላከያ ቅዳሜ በተመሳሳይ 9:00 ሰአት በክልል ስታዲየሞች የሚደረጉ ጨዋታዎች ናቸው።
ኢትዮጵያ ቡና እና ደቡብ ፖሊስ ቅዳሜ 10:00 ሰአት አዲስ አበባ ስታዲየም ላይ ይገናኛሉ።
ሀዋሳ ከተማ ከድሬዳዋ ከተማ እሁድ በ9:00 ሰአት በሀዋሳ ኢንተርናሽናል ስታዲየም ጨዋታቸውን የሚያደርጉ ሲሆን ቅዱስ ጊዮርጊስ ከፋሲል ከነማ ደግሞ በ10:00 ሰአት አዲስ አበባ ስታዲየም ላይ ይጫወታሉ።
በዚህም በተለይ ቅዱስ ጊዮርጊስ መሪነቱን ለማስቀጠል ከፋሲል ከነማ፤ ፋሲል ከነማ ደግሞ ከሜዳው ውጪ ነጥብ ለማግኘትና ደረጃውን ከፍ ለማድረግ የሚገጥሙ መሆናቸው ጨዋታው እንዲጠበቅ አድርጎታል።
ፕሪሚየር ሊጉን ቅዱስ ጊዮርጊስ በ24 ነጥብ አንደኛ ሆኖ ሲመራ ኢትዮጵያ ቡና በ22 ነጥብ፣ ሀዋሳ ከተማ በ21 ነጥብ 2ኛና ሦስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል።
መቀለ ሰብአ እንደርታ፣ ሲዳማ ቡና እና ፋሲል ከተማ በእኩል 20 ነጥብ ከአራት እስከ ስድስተኛ ደረጃን ይዘው ይከተላሉ።
ድሬደዋ ከተማ፣ መከላከያ፣ ደቡብ ፖሊስና ደደቢት ደግሞ ከ13ኛ እስከ 16ኛ ያለውን ደረጃ በመያዝ ወራጅ ቀጠና ላይ ይገኛሉ።
የኮከብ ጎል አግቢነቱን የሀዋሳ ከተማው ታፈሰ ሰለሞንና የአዳማ ከተማ ዳዋ ሁቴሳ እንደዚሁም የሲዳማ ቡናው አዲስ ግደይ በተመሳሳይ 8 ጎሎች ሲመሩ የመከላከያው ምንይሉ ወንድሙ ደግሞ በ7 ጎሎች ይከተላል።