ኤጀንሲው ለአርሶ አደሮች በነፃ መረጃ ለማድረስ የሚያስችል ስምምነት ከሴቭ ዘ ችልድረን ጋር ተፈራረመ - ኢዜአ አማርኛ
ኤጀንሲው ለአርሶ አደሮች በነፃ መረጃ ለማድረስ የሚያስችል ስምምነት ከሴቭ ዘ ችልድረን ጋር ተፈራረመ
አዲስ አበባ ጥር 23/2011 የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኤጀንሲ ለአርሶ አደሮች በነፃ የስርአተ ምግብ መረጃ ማድረስ የሚያስችል ስምምነት ከህፃናት አድን ድርጅት (ሴቭ ዘ ችልድረን) ጋር ተፈራረመ።
ስምምነቱን የተፈራረሙት የኤጀንሲው ዋና ስራ አስፈጻሚ ዶክተር ካሊድ ቦምባ እና በኢትዮጵያ የሴቭ ዘ ችልድረን ዳሬክተር ሚስተር ኢኪን ኦጉቶጉላሪ ናቸው።
የኤጀንሲው ዋና ስራ አስፈጻሚ ዶክተር ካሊድ በስምምነቱ ወቅት እንደገለፁት ከአምስት አመት በፊት የግብርና መረጃዎችን ብቻ ለአርሶ አደሩ ለማስተላለፍ ኤጀንሲው ባስተዋወቀው 8028 ነጻ የስልክ ጥሪ በአራት ክልሎች ተግባራዊ ተደርጓል።
በዚህም በአማራ፣ ኦሮሚያ፣ ትግራይና ደቡብ ክልሎች በሚገኙ 168 ወረዳዎች ላይ ተግባራዊ መደረጉን ገልፀዋል።
ዛሬ የተደረሰው ስምምነት ሴቭ ዘ ችልድረን በስርአተ ምግብ ላይ ያዘጋጃቸውን መረጃዎች በ8028 ነጻ ጥሪ ለአርሶ አደሩ ለማስተላለፍ የሚያግዝ መሆኑን ዶክተር ካሊድ ተናግረዋል።
በኤጀንሲው የ8028 ፕሮጀክት ባለሙያ ወይዘሪት ቅድስት ብዙነህ በበኩላቸው ከሴቭ ዘ ችልድረን ጋር የተደረሰው ስምምነት አርሶ አደሩ የተለያዩ ሰብሎችን አምርቶ እንዲመገብ ተጨማሪ መረጃ የሚያገኝበት ነው ብለዋል።
በመሆኑም አርሶ አደሮች በ8028 በሚያገኙት የስርአተ ምግብ መረጃ የተለያዩ የሰብል አይነቶችን በቀላሉ በማምረትና በመመገብ በሽታዎችን እንዲከላከሉ ያግዛቸዋል።
እንደ ባለሙያዋ ገለፃ ባለፉት አምስት አመታት መረጃ ፈልገው 33 ሚሊዮን 300 ሺህ አርሶ አደሮች ወደ 8028 የደወሉ ሲሆን 4 ሚሊዮን ስልኮች ደግሞ በአሰራሩ ተመዝግበው ይገኛሉ።
በመሆኑም 4 ሚሊዮን አርሶ አደሮችን የስርአተ ምግብ መረጃ ተደራሽ ማድረግ እንደሚቻል በማብራራት በየወረዳው የተመደቡ ባለሙያዎች በቅርበት እርዳታ እንዲሰጡት ይደረጋል ብለዋል።
በተያዘው ዓመት 6 ሚሊዮን አርሶ አደሮችን የአገልግሎቱ ተጠቃሚ ለማድረግ አቅድ መያዙንም ወይዘሪት ቅድስት ገልፀዋል።
የሴቭ ዘ ችልድረን ተወካይ ሚስተር ዳንኤል አቦት ለኢዜአ እንደገለፁት ሴቭ ዘችልድረን በስልጠና እንዲሁም በወረቀት እያስተላለፈ ያለውን የስርአተ ምግብ መረጃ በስምምነቱ መሰረት በቀላሉ በሞባይል ለአርሶ አደሩ ተደራሽ ማድረግ ይችላል።
በቀጣይም የኢትዮጵያ መንግስት በስርአተ ምግብ ላይ በሚሰራቸው ተግባራት አብረው እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል።
ሁለቱ ተቋማት ዛሬ የተፈራረሙት ስምምነት የአሜሪካ የልማት ድርጅት(USAID) ለስርአተ ምግብ ማሻሻያ በሚያደርገው የገንዘብ ድጋፍና በሴቭ ዘችልድረን አማካኝነት ስራ ላይ በሚውል ይሆናል።