'ሳንሹ ካፕ' በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ ሊካሄድ ነው - ኢዜአ አማርኛ
'ሳንሹ ካፕ' በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ ሊካሄድ ነው

አዲስ አበባ ጥር 23/2011 አገር አቀፍ የውሹ የግል የበላይነት የነጻ ፍልሚያ ውድድር (ሳንሹ ካፕ) ለመጀመሪያ ጊዜ ከጥር 26 ቀን 2011 ዓ.ም ጀምሮ መካሄድ ይጀመራል።
ውድድሩ 'ሳንሹ ካፕ' የሚል ስያሜ የተሰጠው የስፖርቱ መጀመሪያ ከሆነችው ቻይና የተገኘ ቃል እንደሆነና ቃሉ ሲተረጎም ነጻ ፍልሚያ የሚል እንደሆነም ተገልጿል።
ለሁሉም ክፍት የሆነው ይህ የውሹ ውድድር በሁለቱም ጾታዎች በራስ ሃይሉ የስፖርት ማዕከል የሚካሄድ ሲሆን ከ100 እስከ 150 ተወዳዳሪዎች ይሳተፉበታል ተብሎ ይጠበቃል።
የግል የበላይነት ውድድሩ በወንዶች ከ48 እስከ 52 ፣ ከ53 እስከ 56 ፣ ከ57 እስከ 60 እና ከ61 እስከ 65 ኪሎ ግራም እንዲሁም በሴቶች ከ48 እስከ 52 ኪሎ ግራም እና ከ53 እስከ 56 ኪሎ ግራም የክብደት ዘርፎች(ካታጎሪ) ይካሄዳል።
የውድድሩ አላማ ውሹ ከሌሎቹ የማርሻል ስፖርቶች የሚለይበትን ነገር ለማሳየትና በስፖርቱ የተሻሉ ተወዳዳሪዎችን ለማፍራት እንደሆነም የኢትዮጵያ ውሹ ፌዴሬሽን የውድድርና ስልጠና ከፍተኛ ባለሙያ አቶ ገበየሁ ሙሉጌታ ለኢዜአ ገልጸዋል።
ውሹ ከሌሎቹ የማርሻል ስፖርቶች የሚለየው እጅና እግርን እኩል በማስተባበርና የተለያዩ መሣሪያዎችን በመጠቀም የሚካሄድ የስፖርት ዓይነት በመሆኑ ውድድሩም ይሄን የማስተዋወቅ ስራ እንደሆነም ተናግረዋል።
ከዚህ በፊት ፌዴሬሽኑ የነጻ ፍልሚያና የአርት(ጥበብ) ውድድሮችን በጋራ ያዘጋጅ እንደነበርና የነጻ ፍልሚያ ውድድር ሲካሄድ ግን ለመጀመሪያ ጊዜ እንደሆነም ተናግረዋል።
ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ከነጻ ፍልሚያ ውድድሩ በተጨማሪ በተያዘው በጀት ዓመት አገር አቀፍ የውሹ የአርት(ጥበብ) ውድድር እንደሚያካሄድም ጠቁመዋል።
በሁሉም የክብደት ዘርፍ ከአንድ እስከ ሶስት የወጡ ተወዳዳሪዎች የሜዳሊያ ሽልማት እንደሚያገኙና እንደየቅደም ተከተላቸው የ5፣ 3 እና 2 ሺህ ብር ሽልማት እንደሚያገኙም አክለዋል።
ውሹ የሚለው ቃል የመጣው ከቻይና ሲሆን “ው” ማለት ወታደራዊ “ሹ” ደግሞ አርት ማለት ነው።
የውሹ ስፖርት በኢትዮጵያ መቼና በማን ተጀመረ ብሎ ለመናገር የሚያስችል የተደራጀ ሰነድ ባይኖርም በስፖርቱ እውቀትና ችሎታው ያላቸው ግለሰቦች በተለያዩ መጠሪያ የውሹ ስፖርትን በኢትዮጵያ አቆጣጠር በ1960ዎቹ ያዘወትሩትና ይለማመዱት እንደነበር መረጃዎች ያመለክታሉ። ኢትዮጵያ ከ2002 ዓ.ም ጀምሮ በአፍሪካና በዓለም አቀፍ ውሹ ፌደሬሽን አባል አገር ናት።