የሸዋ ነገስታት ታሪክን በማስተዋወቅ የቱሪስት መስህብን ለማሳደግ እየተሰራ ነው

ደብረ ብርሃን      ጥር 22/2011 የሸዋ ነገስታት ታሪክን በሃገር ውስጥና በውጭ ሃገራት በማስተዋወቅ የቱሪስት መስህብን ለማጎልበት እየተሰራ መሆኑን የሰሜን ሽዋ ዞን አስታወቀ።

”የኢትዮጵያ ታሪክ በሰሜን ሸዋ ታላቅ የባህልና የታሪክ ሲፖዚየም ” በደብረ ብርሃን ከተማ በመጭው ግንቦት ወር እንደሚካሄድም ተመልክቷል።

ሲፖዚየሙን አስመልክቶ በተካሄደ ህዝባዊ ውይይት የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ተፈራ ወንድምአገኘሁ እንዳስታወቁት የሸዋ ነገስታት ታሪክ  በሀገሪቱ ሊዘነጋ የማይችል ሆኖ ሳለ እስካሁን ትኩረት ሳይሰጠው ቆይቷል።

እውነተኛን ታሪክ በማጠልሸት የሸዋ ታሪካዊ፣ ባህላዊና ፖለቲካዊ እሴቶች ከሌሎች የኢትዮጵያ ህዝቦች ጋር ያለውን መልካ ምድራዊ፣ ማህበራዊና ሃይማኖታዊ ትስስሮች ተዛብተው መኖራቸውን ተናግረዋል።

በዚህም በአካባቢው ያሉ የነገስታት መቀመጫ ስፍራዎች ለቱሪስት መስህብ ሳይውሉ ተዳፍነው መቆየታቸው ገልጸው በአሁኑ ወቅት ታሪካዊነታቸው ተጠብቆ የቱሪስት መዳረሻ እንዲሆኑ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

አቶ ተፈራ እንዳሉት በአካባቢው እያደገ የመጣው የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ ከአካባቢው ታሪክ ጋር በማስተሳሰር የቱሪዝም ዘርፉን ለማሳደግ ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል።

ባለፉት ስድስት ወራት ብቻም 10 ነጥብ 9 ቢሊዮን ብር ካፒታል ያስመዘገቡ 194 ባለሀብቶች ትላልቅ ኢንዱስትሪዎችን ለመገንባት የሚያስችል ፈቃድ መውሰዳቸውን ተናግረዋል።

ቀደም ሲልም ከ1 ሺህ 800 በላይ ባለሃብቶች ወደ አካባቢው መጥተው እያለሙ መሆናቸውን የገለፁት አስተዳዳሪው ይህም የቱሪዝም ዘርፉ ጠንካራ መሰረት እንዲኖረው የሚያግዝ መሆኑን ገልጸዋል።

"አሁን በሀገሪቱ የተጀመረው የአንድነት፣ የመደመርና የፍቅር ጉዞ ይበልጥ ጎልብቶ የሸዋ ታሪክ በሀገሪቱ ጎልቶ እንዲወጣ በተሳሳተ መንገድ ሲተረክ የኖረውን ታሪክ ማስተካከል ይገባል" ብለዋል።

ለእዚህም ከመጪው ግንቦት 10 እስከ 12 ቀን 2011ዓ.ም ታላቅ የባህልና የታሪክ ሲፖዚየም በደብረብርሃን ከተማ ለማዘጋጀት ከወዲሁ የንቅናቄ ሥራ መጀመሩን አስረድተዋል።

"በሲምፖዚየሙ የሽዋ ነገስታት ታሪክን የሚዘክር ጥናታዊ ጽሁፍ በሃገር ውስጥና በውጭ ሃገራት ምሁራን ይቀርባል" ሲሉም ጠቁመዋል።

ሲምፖዚየሙ የተሳካ እንዲሆንና የሽዋ ታሪክ ጎልቶ እንዲነገር የአካባቢው ተወላጆችና ምሁራን ከወዲሁ ድጋፍና እገዛ እንዲያደርጉም ጥሪ አቅርበዋል።

የደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ኃይለማሪያም ብርቄ በበኩላቸው ለሲፖዚየሙ የሚሆኑ በጥናትና ምርምር የሚደገፉ እውነታዎችን ለዓለም ሀዝብ ለማስተዋወቅ ተቋሙ የበኩሉን እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

በቅርቡ የሚከበረውን የአደዋ በዓልን ጨምሮ በቀጣይም የሚካሄዱ የባህል ሲፖዚየምና የጥናትና ምርምር ሲፖዚየሞች በሸዋ ታሪክ ላይ አተኩረው እንደሚካሄዱም አስታውቀዋል።

የሰሜን ሸዋ ዞን አባት አርበኞች ዋና ፀሐፊ አቶ ተፈራ ወልደአማኑኤል በበኩላቸው አባቶቻችን ሀገርን ከውጪ ጠላት ለመከላከል ካደረጉት ተሳትፎ  በተጨማሪ ለሀገሪቱ ስልጣኔ የጣሉት መልካም አሻራ ተዘንግቶ በመቆየቱ በአርበኛው ቤተሰብ ዘንድ ቁጭት ፈጥሮ መቆየቱን ተናግረዋል።

የአርበኞች ቤተሰቦች በሸዋ ነገስታት ታሪክ ላይ ጥናትና ምርምር ከሚያካሂዱ ተቋማት ጋር ተቀናጅተው በመስራት የሸዋ ስልጣኔን ለመመለስ እንደሚሰሩም አመልክተዋል።

በውይይቱ ከ100 በላይ የሚሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎችና የታሪክ ተመራማሪዎች ተሳትፈዋል ሲል የዘገበው ኢዜአ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም