የማዕድንና ነዳጅ ሚኒስቴር የፖሊሲ ማሻሻያና የ25 ዓመት ፍኖተ ካርታ እያዘጋጀ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የማዕድንና ነዳጅ ሚኒስቴር የፖሊሲ ማሻሻያና የ25 ዓመት ፍኖተ ካርታ እያዘጋጀ ነው
አዲስ አበባ ጥር 22/2011 በማዕድንና ነዳጅ ዘርፍ ችግሮችን ለመፍታት የፖሊሲ ማሻሻያ እያደረገ መሆኑን የማዕድንና ነዳጅ ሚኒስቴር ገለጸ።
ሚኒስትሩ ዶክተር ሳሙኤል ኡርካቶ በተለይ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደገለጹት በማዕድን ዘርፍ የሚስተዋሉ የአሰራር ችግሮችን ለመፍታት የፖሊሲና ህግ ማሻሻያዎች እየተደረጉ ነው።
የኢትዮጵያ ማዕድን ፖሊሲ ረቂቅ ተዘጋጅቶ ለባለሙያዎችና ለሚመለከታቸው አካላት ለውይይት ሊቀርብ መሆኑንም አንስተዋል።
ኢትዮጵያ ካሁን በፊት ያልነበራትን የነዳጅ ፖሊሲ ረቂቅ በማዘጋጀት በተመሳሳይ ለውይይት ሊቀርብ መሆኑን የጠቀሱት ሚኒስትሩ፤ በፖሊሲውም በዘርፉ የሚስተዋሉ የአስተዳደርና ሌሎች ችግሮች ይፈታሉ ተብሎ እንደሚጠበቅም ገልጸዋል።
ሁለቱ ፖሊሲዎች ሰፊ ውይይት ከተደረገባቸው በኋላ ለካቢኔ ቀርበው ሲጸድቁ ስራ ላይ እንደሚውሉም አብራርተዋል።
በተመሳሳይ በ1976 የተዘጋጀው የኢትዮጵያ ነዳጅ ሰራዎች ማሻሸያ አዋጅ ለአሰራር አመቺ ባለመሆኑና ከወቅቱ ጋር ባለመሄዱ ማሻሻያ እየተደረገበት ነው ብለዋል።
እንደ ሚኒስትሩ ገለጻ የስነ ምህዳር መረጃ በማደራጀት የማዕድንና ነዳጅ መጠንን ለይቶ ኢንቨስትመንትን ለመሳብም እየተሰራ ነው።
በዚህም ያለውን የማዕድን አለኝታ በማወቅና ወደ ኢንቨስትመንት በመቀየር ከውጭ የሚገቡ በርካታ የማዕድን ግብአቶችን መተካት ያስችላልም ብለዋል።
የማዕድን ዘርፍ አቅም ግንባታ ምክትል ዳሬክተር አቶ ያሬድ ፈቃደ በበኩላቸው የማዕድን ዘርፉን አውቆ በትክክል ለመምራት የ25 ዓመት የማዕድን ፍኖተ ካርታ ለማዘጋጀትም ቅድመ ዝግጅት እየተደረገ ነው።
የማዕድን ዘርፍ የሚመራበት የራሱ ስትራቴጂ አለመኖርም በሚፈለገው መጠን ውጤታማ እንዳይሆን ማድረጉን አብራርተዋል።
ፍኖተ ካርታው ዘርፉ የሚጠበቅበትን ተግባራት በግልጽ በማስቀመጥና ስራዎችን በተደራጀና ዘመናዊ በሆነ መንገድ ለመምራት ያግዛል ሲሉም አቶ ያሬድ ገልጸዋል።
ለፍኖተ ካርታው የሚያስፈልጉ ቅድመ ጥናቶች ተጠናቀው ሙሉ የማስተር ፕላን ስራው በቀጣዩ ስድስት ወራት ውስጥ እንደሚጀመር ገልጸው በ2012ዓ.ም ወደ ትግበራ ይገባል ብለዋል።
በፍኖተ ካርታ ዝግጅቱ ዩኒቨርሲቲዎች፣ ኩባንያዎች፣ ክልሎችና ሌሎች ባለሙያዎችም ይሳተፉበታል ተብሏል።
በኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት 60 ኩባንያዎች በማዕድን ልማትና ምርት፣ 76 በፍለጋ እንዲሁም 5 ኩባንያዎች ደግሞ በነዳጅ ስራ የተሰማሩ መሆናቸውን ከማዕድንና ነዳጅ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያሳያል።