በድሬዳዋ ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት ለመፍጠር ኃላፊነታችንን እንወጣለን ...የአገር ሽማግሌዎችና የኃይማኖት መሪዎች - ኢዜአ አማርኛ
በድሬዳዋ ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት ለመፍጠር ኃላፊነታችንን እንወጣለን ...የአገር ሽማግሌዎችና የኃይማኖት መሪዎች
ድሬዳዋ ጥር 22/2011 በድሬዳዋ አስተዳደር አንድነትና ፍቅር እንዲመለስ፣ ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት ለመፍጠር ኃላፊነታቸውን እንደሚወጡ የአገር ሽማግሌዎችና የኃይማኖት ተቋማት አመራሮች አረጋገጡ፡፡
የድሬዳዋ ጊዜያዊ የፀጥታ ኮሚቴ ሰብሳቢ ''ለሰላምና ለሕዝቦች ዘላቂ አንድነት መምሰል ሳይሆን፤መሥራት ያስፈልጋል'' ብለዋል፡፡
የአገር ሽማግሌዎች፣ የኃይማኖት ተቋማት አመራሮችና የሕዝብ ተወካዮች ትናንት ከኮሚቴው አመራሮች ጋር ባደረጉት ውይይት ማጠቃለያ ላይ እንዳመለከቱት በአስተዳደሩ ሰላምንና መረጋጋትን በማስፈን ድርሻቸውን ይጫወታሉ።
ለሰላምና መረጋጋት ፣ ለሕዝቦች አንድነትና የጋራ ዕድገት ተቀናጅተው እንደሚሰሩም አስታውቀዋል፡፡
የአገር ሽማግሌው አቶ ዩሱፍ ሙሣ አንዳንድ አመራሮች ሞት፣መፈናቀል፣የንብረት ውድመትና ዘረፋን በማስፋፋት እጃቸው እንዳለበት ገልጸዋል።አገርንና ሕዝብን እርስ በርስ ማጋጨትን ሥራ አድርገው መያዛቸውን ይገልጻሉ።
''የድሬዳዋ በሽታ የአስተዳደሩ ብልሹነት ነው።ይህ ከታከመ መፍትሄ ይመጣል'' ብለዋል።
ለአካባቢው መበጥበጥ በገጠርና በመልካ ጀብዱ ቀበሌ ለሰዎች ሕይወት መጥፋት መንስኤ እየሆነ ያለው መንግሥት ያስታጠቀውና ለብሄሩ ዘብ የሆነው ሚሊሺያ ጉዳይ አስቸኳይ መፍትሄ ይሻል ያሉት አቶ መሐመድ ሁሴን ናቸው፡፡
በየአካባቢያችን ሰላም እንዲሰፍን፣ የሕዝቦች ፍቅርና አንድነት እንዲጎለብትና ወጣቶች በሕገ-ወጥ ተግባራት እንዳይሰማሩ ተደራጅተው እያስተማሩ መሆናቸውንም ተናግረዋል።
ወጣት አብዱልአዚዝ ዩሱፍ በበኩሉ በቀበሌ 01ና 09 በተደጋጋሚ እየተከሰተ ለሚገኘው ችግር አስተዳደሩ ዘላቂ መፍትሄ እንዲሰጠው ጠይቋል፡፡
''ወጣቶች አገር አቀፍ ለውጡን ተቀብለን ለውጡ እንዳይደናቀፍ እየሰራን እንገኛለን። ለአካባቢያችን ሰላምና ፀጥታ መከበር ኃላፊነታችንን እንወጣለን'' ብሏል፡፡
አቶ ሻሜ አህመድ የተባሉ ነዋሪ በበኩላቸው ሰላም መተኪያ የሌለው ውድ ሃብት በመሆኑ፤ ሕዝቡ መሠረታዊ የሆነውን ሃብት እንዲጠብቀው ጠይቀዋል፡፡
በአስተዳደሩ አስተማማኝ ሰላምና ዘላቂ መረጋጋት ለመፍጠር በየደረጃው የሚገኙ አጥፊ አመራሮች በሕግ መጠየቅ አለባቸው ሲሉም አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡
''እኛ የአካባቢያችን ሰላም መጠበቅና የዱሮ ፍቅርና አንድነታችን መመለስ እንችላለን። ለዚህም በኃላፊነት እንሰራን'' ብለዋል፡፡
ሌላው አስተያየት ሰጪ አቶ ሙስጠፋ ዓሊ በከተማው አገራዊ ለውጡን የማይፈልጉ አባላትና ያልሆነ ወሬ በማሰራጨት ሕዝቡን ስጋት ውስጥ በሚከቱ አመራሮችና ቡድኖች ጥብቅ ቁጥጥር እንዲደረግ ጠቁመዋል፡፡
የሸምግልናን ተግባራት የሚያደናቅፉ አካላትን ለሕግ ማቅረብና የአካባቢውን ሰላምና ፀጥታ መመለስ እንደሚያስፈልግም አመልክተዋል፡፡
የድሬዳዋ ጊዜያዊ የጸጥታ ኮሚቴ ሰበሳቢና የምሥራቅ ዕዝ ምክትል አዛዥ ብርጋዲዬር ጄኔራል ተስፋዬ ወልደማርያም የድሬዳዋ ነዋሪዎች በጎሳና በብሔር ተከፋፍለው ከመጋጨትና ለውጡን ለማደናቀፍ ለሚንቀሳቀሱ አካላት መሣሪያ መሆን እንደሌለባቸው አሳስበዋል።
ነዋሪዎቹ የቀድሞ ኅብረታቸውን፣ፍቅራቸውን፣ ሰላምና ወዳጅነታቸውን ማጠናከር ይገባቸዋል ብለዋል፡፡
የአገር ሽማግሌዎቹና የኃይማኖት አባቶቹ አገራዊው ለውጥ እንዲሳካ ሰላምን በማስጠበቅ ግንባር ቀደም ሆነው እንዲሰሩም ጠይቀዋል።
''ሽምግልናን መምሰል ሳይሆን መሆንና መተግበርን ይሻል፣ የኃይማኖት አባት መምሰል ሳይሆን መሆን ይገባል'' ሲሉም መልዕክታቸውን አጠናክረውታል፡፡
የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ ኢብራሂም ዑስማን የትኛውም ግለሰብም ይሁን አመራር አጥፍቶ ከተገኘ በሕግ እንደሚጠየቅ አስታውቀዋል።
ብሄርን ተገን አድርጎ ወንጀል የሚፈጽም የሚሊሺያ ኃይል አፋጣኝና አስቸኳይ እርምት እርምጃ ይወሰድበታል ብለዋል፡፡