ቀጥታ፡

በግል ባለሀብቱ የሚከናወኑ ግዙፍ የልማት ፕሮክጅቶች የአገሪቷን የብድር ጫና ይቀንሳሉ-ምሁራን

አዲስ አበባ ጥር 22/2011 በመንግስትና የግል አጋርነት የሚሰሩ ግዙፍ የመሠረተ ልማት ፕሮጀክቶች በአግባቡ ከተመሩ የአገሪቷን የብድር ጫና እንደሚቀንስ የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች ተናገሩ።

የኢትዮጵያ መንግስት ግዙፍ የመንገድና የኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶች አቅም ባላቸው ባለሀብቶች እንዲገነቡ ይፋ ማድረጉ ይታወቃል።

ይህን የሚከታተል ተቋም በገንዘብ ሚኒስቴር ስር ተቋቁሞ ሥራ የጀመረ ሲሆን በከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት የሚመራ 9 አባላት ያሉት ኮሚቴ ተደራጅቷል።

የምጣኔ ሀብትና የግብይት ባለሙያዎች እንደሚሉት ባለፉት ዓመታት በመንግስት የተጀመሩ የመሠረተ ልማት ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው የጊዜ ገደብና ጥራት አልተጠናቀቁም።

መንግስት ለተጀመሩ የመሠረተ ልማት ፕሮጀክቶች ማስፈጸሚያ ከዓለም የገንዘብ አበዳሪ ተቋማት ብድር የወሰደ ሲሆን ፕሮጀክቶቹ በተያዘላቸው የጊዜ ገደብ ባለመጠናቀቃቸው አጠቃላይ የአገሪቷ የብድር ጫና 50 ቢሊዮን ዶላር መድረሱን ከገንዘብ ሚኒስቴር የተገኙ መረጃዎች ያመለክታሉ።

ለፕሮጀክቶቹ መዘግየት እንደ ምክንያት ከሚጠቀሱት ጉዳዮች ውስጥ የፕሮጀክት አስተዳደር አቅም ማነስ፣ ውጤታማ የቡድን ስራ አለመኖር እንዲሁም የባለድርሻ አካላት ቅንጅት ማነስ ተጠቃሽ ናቸው።

የምጣኔ ሀብት ባለሙያ ዶክተር ተሾመ አዱኛ እንዳሉት ግዙፍ የመሠረተ ልማት ፕሮጀክቶች በግል ባለሐብቶች እንዲገነቡ መደረጉ የአገሪቷን ልማት ከማፋጠን ባሻገር የዕዳ ጫናን ለመቀነስ የሚያስችል አዋጭ የልማት መንገድ ነው። 

''መንግስት ኢኮኖሚውን ተቆጣጥሮ ያደገበት አገር የለም'' ያሉት ዶክተር ተሾመ፤ በበርካታ አገራት የተከናወኑ የልማት ስራዎች የግል ባለሀብቱ ተሳትፎ የታከለበት በመሆኑ ለስኬት እንደበቁም ገልጸዋል።

መንግስት ከባለሀብቶች ጋር ከሚያደርገው የልማት ስምምነት በተጨማሪ ጠንካራ አማካሪና የጥራት ተቆጣጣሪ ሊኖረው እንደሚገባም ዶክተር ተሾመ ገልጸዋል።

የግብይት ባለሙያው ዶክተር ጌቴ አንዱዓለም በበኩላቸው በግል ባለሀብቶች የሚገነቡ ፕሮጀክቶች ጥንቃቄ በተሞላበት መንገድ የሚከናወኑ ከሆነ የአገሪቷን ምጣኔ ሀብት ለመደገፍ ከፍተኛ ጠቀሜታ አላቸው ብለዋል።

ግዙፍ የመንገድና የኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶች በግል ባለሀብቶች እንዲገነቡ መደረጉም መንግስት በሌሎች ልማቶች ላይ እንዲያተኩር የሚረዳ መሆኑን አብራርተዋል።

በግል ባለሀብቱ እውቀትና ገንዘብ የሚገነቡ የልማት ፕሮጀክቶች መንግስት ከዚህ በፊት የገጠመውን ችግር እንዳይደግም የሚያስችል መሆኑንም አስረድተዋል።

በፕሮጀክቶች ትግበራ ላይ ኢትዮጵያውያን ባለሀብቶችን ማሳተፍና ማበረታታት ለአገር ምጣኔ ሀብት ዕድገት ከፍተኛ ፋይዳ ይኖረዋልም ብለዋል።

የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ተሾመ ታፈሰ እንዳሉት መንግስት ባቋቋማቸው ኮሚቴዎች አማካይነት የተጠኑና ውሳኔ ያገኙ ስድስት የኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶች ግንባታ በቅርቡ በጨረታ ለግል ባለሀብቶች ያስተላልፋል።

በ795 ሚሊዮን ዶላር ወጪ 798 ሜጋ ዋት ኃይል የሚያመነጩ ስድስት የኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶች የአዋጭነት ጥናት ተጠናቆ ወደ ጨረታ ሂደት የሚያስገባቸው ተግባርም እየተከናወነ ይገኛል።

መንግስት ፕሮጀክቶቹ በግል ባለሀብቱ እንዲከናወን ያደረገበት ዋና ምክንያትም የህዝብ አገልግሎትን በፍጥነትና በጥራት ለማከናወን፣ ኢንቨስትመንትን ለማስፋፋት እንዲሁም እያደገ የመጣውን የህዝብ ፍላጎት ለመመለስ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም