ባሳለፍነው ስድስት ወራት ለታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ 484 ሚሊዮን ብር ተሰብስቧል - ኢዜአ አማርኛ
ባሳለፍነው ስድስት ወራት ለታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ 484 ሚሊዮን ብር ተሰብስቧል
አዲስ አበባ ጥር 22/2011 ባለፉት ስድስት ወራት ለህዳሴ ግድብ ከ484 ሚሊዮን ብር በላይ መሰብሰቡን የግድቡ ህዝባዊ ማስተባበሪያ ምክር ቤት ፅህፈት ቤት አስታወቀ።
ተቀዛቅዞ የነበረውን የድጋፍ ተሳትፎ ለማሳደግም እየተሰራ ነው።
የግድቡን ስራዎች አጠናክሮ ማስቀጠል በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ ፅህፈት ቤቱና የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ማህበር የጋራ መግለጫ ሰጥተዋል።
የፅህፈት ቤቱ የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ኃይሉ አብረሃም በበጀት ዓመቱ 900 ሚሊዮን ብር ለመሰብሰብ ታስቦ በግማሽ ዓመቱ 484 ሚሊዮን ብር በላይ መሰብሰብ መቻሉን ገልፀዋል።
በሜቴክ አማካኝነት በተፈጠረ ችግርና ተያያዥ ጉዳዮች ግድቡ መጓተቱን ተከትሎ ከነሃሴ ወር ወዲህ የህብረተሰቡ ተሳትፎ ቀንሶ ቢቆይም ለውጡ ላይ ባለ እምነትና መረጃዎችን በግልፅ ለህብረተሰቡ ተደራሽ የማድረግ ስራ በመሰራቱ ለግድቡ የሚደረገው ድጋፍ ባለፉት ሁለት ወራት እየጨመረ መምጣቱን ተናግረዋል።
ተቀዛቅዞ በመቆየቱም ሃምሌ ላይ ተሰብስቦ የነበረው 138 ሚሊዮን ብር ነሃሴ ላይ ወደ 52 ሚሊዮን ዝቅ ብሎ መታየቱ ማሳያ እንደነበር ገልፀዋል።
የሚመለከታቸው የመንግስት አካላት በጥናት ላይ የተመሰረተ መረጃ ለህዝቡ ካስተላለፉና ጠቅላይ ሚኒስትሩም ግንባታውን መጨረስ አገራዊ ኃላፊነትን መወጣት መሆኑን ካሳሰቡ በኋላ በታህሳስ መጨረሻ ድጋፉ 484 ሚሊዮን ብር መድረሱን ጠቅሰዋል።
በዓመቱ መጨረሻ የህብረተሰቡን አጠቃላይ ድጋፍ ከ12 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር ወደ 13 ቢሊዮን ብር ለማሳደግ የታቀደ ሲሆን በግማሽ ዓመቱ የታቀደውን ያህል እንደተገኘ ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል።
ተሳትፎውን ለማሳደግም ተቋርጠው የነበሩ የቅስቀሳ መድረኮች እስከታችኛው ህብረተሰብ እየተከናወኑ ያሉ መሆኑን ገልፀው፤ ወቅታዊ መረጃዎችንም በማድረስ ተሳትፎው እንዲመለስ እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።
ከተሳትፎ ባለፈም የግድቡን ተፋሰስ ከአደጋ ለመጠበቅ እንቦጭን ማስወገድና የአፈር እቀባ ስራዎችም እየተሰሩ እንደሚገኙ ነው አቶ ኃይሉ ያስታወቁት።
አሁን ግድቡ ያለው አፈፃፀም 65 በመቶ ላይ ነው ያሉት አቶ ኃይሉ ስራው በሚቀጥሉት አራት አመታት እንደሚጠናቀቅ ተጠንቶ በሜቴክ ፈንታ ለውጪ ተቋራጮች የተሰጠ መሆኑንም አስረድተዋል።
ፅህፈት ቤቱ እስካሁን ገንዘብ የማሰባሰብ ስራ ብቻ ይሰራ የነበረ ሲሆን አሁን ግን ያሉ ሂደቶችን የመጠየቅና መረጃ መስጠት እንዲችል መተማመን ላይ መደረሱንም ገልፀዋል።
ከአሁን በኋላም ያሉ እውነተኛ መረጃዎች ለህዝቡ እየተገለጹ እንደሚቀጥሉም ጠቅሰዋል።
በግድቡ ላይ የህዝብ ገንዘብ ያባከኑና የወሰዱ ግለሰቦችና ተቋማትም አስፈላጊው እርምጃ ይወሰድባቸዋል ብለዋል።
የዳያስፖራ ማህበር ዳይሬክተር አቶ አብርሃም ስዩም በበኩላቸው የህዳሴ ግድብ መጠናቀቅ የኢትዮጵያን ክብርና ታላቅነት የማሳየት ጉዳይ በመሆኑ ያሉ ችግሮችን ፈትቶ ግድቡን ለማጠናቀቅ የዳያስፖራው ድጋፍ ከቀድሞ በተሻለ ሊነሳሳ ይገባል ብለዋል።
ከዚህ ቀደም በዳያስፖራው የተደረገው ድጋፍ ካለው የዳያስፖራ ቁጥር አንፃር አመርቂ አልነበረም ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፤ ቀድሞ በነበረው መንግስት ላይ እምነት የሌላቸው መኖራቸውና የግድቡም አካሄድ ግልፅነት የጎደለው በመሆኑ በበቂ ላለማዋጣት ምክንያት እንደነበር አንስተዋል።
ማህበሩ በአገር ውስጥ ካለው ዳያስፖራ ጋር ነገ በራስ ሆቴል ውይይት የሚያደርግ ሲሆን በግድቡ ላይ ያሉ ጥያቄዎች ተመልሰው ዳያስፖራው የሚያደርገው ድጋፍ የሚጠናከርበት እንደሚሆንም ነው ያስረዱት።
ግድቡ 35 በመቶ ብቻ የቀረው በመሆኑ ይህንን ሁሉም ኢትዮጵያዊ ርብርብ አድርጎ በማጠናቀቅ የጀመረውን አሻራ የማስቀመጥ ስራንም ከግብ ማድረስ እንዲያጠናክር አቶ አብርሃም ጠይቀዋል።