ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ የሽግግር ምክር ቤት በኢትዮጵያ ብሔራዊ መግባባትና እርቀ ሰላም እንደሚያስፈልግ ገለጸ

አዲስአበባ ጥር 21/2011 የኢትዮጵያ ብሔራዊ የሽግግር ምክር ቤት በኢትዮጵያ አንዳንድ አካባቢዎች የሚታየውን አለመረጋጋት ለማስወገድ ብሔራዊ መግባባትና እርቀ ሰላም ማድረግ እንደሚያስፈልግ ገለፀ።

የምክር ቤቱ ሊቀ መንበር አቶ ስለሺ ጥላሁን እንደገለጹት በተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል ያለው ልዩነት እንደተጠበቀ ሆኖ በኢትዮጵያ ብሔራዊ መግባባትና እርቅን መሠረት ያደረገ አገር አቀፍ ጉባዔ እንዲካሄድ ከተለያዩ ፓርቲዎች ጋር የጋራ ስራ ተጀምሯል።   

የምክር ቤቱ ሁሉን አቀፍ ብሄራዊ መግባባትና እርቀ ሰላም እንዲካሄድ ዓለም አቀፍ አስተባባሪ ኮሚቴ አቋቁሞ ሲሰራ መቆየቱንም ገልጸዋል።

ከዚህ በፊት 26 የፖለቲካ ፓርቲዎችና 23 የሲቪክ ማህበራትን ያካተተ የምክክር መድረክ በሲያትል ሲያካሂድ መቆየቱን አቶ ስለሺ ተናግረዋል።

ምክር ቤቱ ዛሬ በአዲስ አበባ ያካሄደው የምክክር መድረክ ዓላማም በአገሪቱ ብሔራዊ መግባባትና እርቅ ሰላም ለማካሄድ በተጀመረው እንቅስቃሴ ሌሎች ፓርቲዎችም እንዲሳተፉ ለማድረግ ነው ብለዋል።

በመሆኑም በአገሪቱ ብሄራዊ መግባባት ለመፍጠርና እርቅ ለማካሄድ በተጀመረው እንቅስቃሴ ሌሎች የፖለቲካ ፓርቲዎችም እንዲሳተፉ ጥሪ አቅርበዋል።

ለመደመርና በአገሪቱ ዘላቂ ሰላም ለማምጣት ብሄራዊ መግባባትና እርቀ ሰላም ማካሄድ አስፈላጊ መሆኑንም አቶ ስለሺ አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም