በማህበራዊ ትረስት ፈንድ አማካኝነት ዜጎችን ከጎዳና ላይ የማንሳት ስራ ሊጀመር ነው - ኢዜአ አማርኛ
በማህበራዊ ትረስት ፈንድ አማካኝነት ዜጎችን ከጎዳና ላይ የማንሳት ስራ ሊጀመር ነው
አዲስ አበባ ጥር 21/2011 የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አዲስ ባቋቋመው ማህበራዊ ትረስት ፈንድ አማካኝነት በቀጣዮቹ ሳምንታት በጎዳና ላይ የሚኖሩ ዜጎችን በማንሳት ወደ ስድስት የተለያዩ ማዕከላት ሊያስገባ ነው።
የአስተዳደሩ ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ በቀጣዮቹ ሳምንታት ቁጥራቸው 50 ሺህ የሚሆኑ ዜጎችን ከጎዳና ላይ የማንሳት ስራ ይከናወናል።
ኑሯቸውን በጎዳና ላይ ያደረጉ እነዚህን ዜጎች በማንሳትም ወደ ተዘጋጁላቸው ስድስት የተለያዩ ማዕከላት እንዲገቡ ይደረጋልም ብለዋል።
በክንውኑ ሂደት ሴቶችና ህጻናት ቅድሚያ የሚያገኙ ሲሆን ሌሎችም በቀጣይ ጊዜያት ወደ ማዕከላቱ እንዲገቡ ይደረጋል ብለዋል።
ከተማ አስተዳደሩ በመነሻነት ለትረስት ፈንዱ ማቋቋሚያነት የሚያግዝ 100 ሚሊዮን ብር መመደቡንና የኢትዮጵያ አየር መንገድም አንድ ትኬት ሲቆረጥ አንድ ብር ገቢ ለማድረግ ቃል ገብቷል ብለዋል።
ኢትዮ ቴሌኮምም ከሚሰጠው አገልግሎት ላይ ለትረስት ፈንዱ ድጋፍ እንደሚያደርግም ጠቁመዋል።
ከአርቲስቶች መካከል እስካሁን ብሩክታዊት ጌታሁን (ቤቲጂ)፣ቴዎድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ)፣ አጫሉ ሁንዴሳና ጎሳዬ ተስፋዬ ኮንሰርት በማዘጋጀት ገቢውን በሙሉ ለትረስት ፈንዱ ገቢ ለማድረግ ቃል ገብተዋል።
ከአገር ውጪ ያሉ አርቲስቶችም ለትረስት ፈንዱ ድጋፍ እንደሚያደርጉ ቃል መግባታቸውንና ከአገር ውጪ ያሉ ዜጎችም ድጋፍ ማድረግ እንደሚችሉ አመልከተዋል።
ለትረስት ፈንዱ የገንዘብ ማሰባሰቢያ አማራጭ እንዲሆንም በአጭር የጽሁፍ መልዕክት መላኪያ 6400 እና በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ “የባንክ ሂሳብ ቁጥር 1000272444726” ድጋፍ ማደረግ ይቻላል ተብሏል።
የማህበራዊ ትረስት ፈንዱ በዘላቂነት ለዜጎቹ የስራ እድል ፈጥሮ ራሳቸውን እንዲችሉ ተሳቢ ያደረገ እንደሆነና ይህም ዜጎች ህልማቸውንና ተስፋቸውን ማሳካት እንዲችሉ የበኩሉን አስተዋጽኦ ያበረክታል ብለዋል።
የከተማው ህዝብ ፣ የእምነት ተቋማት ፣ የልማት ድርጅቶች እና የሚዲያ ባለሙያዎች በቻሉት ሁሉ ትረስት ፈንዱን በመደገፍ ግዴታቸውን እንዲወጡም ምክትል ከንቲባው አሳስበዋል።
ትረስት ፈንዱን የሚያስተባበር 15 አባላትን የያዘ ቦርድ መቋቋሙም ታውቋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የጎዳና ላይ ነዋሪዎችን በዘላቂነት ለማቋቋም የማህበራዊ ትረስት ፈንድ የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሳህለ ወርቅ ዘውዴ በተገኙበት ይፋ ማድረጉ ይታወሳል።