ቀጥታ፡

የአባይ ተፋሰስ የትብብር ማዕቀፍ ስምምነት ተግባራዊ እንዲሆን የውጭ ጉዳይ ሚነስቴር በትኩረት ሊሰራ ይገባል - የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት

አዲስ አበባ  ጥር 21/2011 የአባይ ተፋሰስ የትብብር ማዕቀፍ ስምምነት የፈረሙ አገራት ተግባራዊ እንዲያደርጉና ያልፈረሙ አገራት እንዲፈርሙ ለማድረግ የውጭ ጉዳይ ሚነስቴር በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባ የህዝብ ተወካዮች ምክርቤት  አሳሰበ።

በምክር ቤቱ የውጭ ጉዳይ ግንኙነትና ሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ተስፋዬ ዳባ እንደገለጹት የአባይ ተፋሰስ ስምምነት የፈረሙ አገራት ስምምነቱን እንዲያጸድቁና ያልፈረሙት ደግሞ እንዲፈርሙ በማድረግ በኩል ጥሩ እንቅሰቃሴዎች ቢኖሩም አሁንም የሚንስቴሩን ልዩ ትኩረት የሚሻ ስራ ነው።

በቢዝነስና ኢኮኖሚ መስክ የብድርና እርዳታ መጠን እያደገ መምጣቱ፣ የትብብር ፍላጎት ያሳዩ አገራት ቁጥር መጨመሩ፣ በአፍሪካ ቀንድ ሰላም ለማስፈን በአገሪቷ እየተከናወኑ ያሉ ተግባራትና ከኤርትራ ጋር የተደረገው እርቅ በሚንስቴሩ  ከተከናወኑ ስራዎች መካካል በቋሚ ኮሚቴው በጥንካሬ ታይተዋል።

የዳያስፖራው ማህበረሰብ ተሳትፎን ለማሳደግ እየተሰሩ ያሉ ስራዎች፣ በውጭ አገራት በእስር የሚገኙና በህገ ወጥ መንገድ ከአገር የወጡ ዜጎች ወደ አገራቸው መመለሳቸውና ሌሎች ስራዎችም ለአብነት ተነስተዋል።   

የሚንስቴሩ የስድስት ወራት የመደበኛ 34 በመቶና የካፒታል 26 በመቶ በጀት አፈጻጸም ዝቅተኛ በመሆኑ ማሻሻል እንደሚገባ የተገለጸ ሲሆን፤ በኦዲት ግኝቶች ላይ ያሉ ክፍተቶች ከችግሮቹ ስፋትና ከዓመታት መደራረብ አንጻር ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ ሊፈቱ እንደሚገባቸውም ቋሚ ኮሚቴው አሳስቧል።

ከምክር ቤቱ አባላት የዲፕሎማቶች፣ የሚሲዮኖችና የድጋፍ ሰጪ ሰራተኞች ምደባ ምን ያህል በብቃት ለይ የተመሰረተ፣ ከአድሎ ነጻ የሆነና ፍትሃዊ ነው? የሚሉት ጥያቄዎች ተነስተው፤ በዚህ በኩል በሕብረተሰቡ በኩል ስጋት መኖሩም ተነስቷል።

ከኤርትራ ጋር የሚደረገው ስምምነት መዘግየት፣ የባህረ ሰላጤው አገራት ለአገሪቷ ስጋት እንዳይሆኑ ማድረግ፣ በሱዳን በኩል ወደ ኢትዮጰያ እየገቡ ያሉ ህገ ወጥ የጦር መሳሪያዎች እና የአገሪቷን ድንበር ጥሰት ለመከላከልና ከኢትዮጵያ ተመዝብሮ በውጭ አገራት የሚገኘውን ሀብት ለማስመለስ በሚንስቴሩ በኩል ምን እየተሰራ ነው? የሚሉ ጥያቄዎችም ተነስተዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚንስትሩ ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ በሰጡት ምላሽ ከአባይ ተፋሰስ አገራት ጋር የሚደረጉ ስምምነቶችን በተመለከተ አገሮችመ ከጥቅማቸው አንጻር የሚያዩ በመሆኑና የግብፅ ተጽዕኖ በመኖሩ  የዲፕሎማሲ ስራው ብዙ ጊዜና ጥረት የሚጠይቅ ነው ብለዋል።

በቀጣይም ኢትዮጵያ አገሮቹ ላይ ተጽዕኖ የማድረግ አቅሟ እየተጠናከረ ሲሄድ የተሻለ እንደሚሆን ገልጸው 'ተስፋ አስቆራጭ ሁኔታ አይደለም'  ሲሉም ተናግረዋል ሚንስትሩ።

የዲፕሎማቶች ብቃት አንጻራዊ መሆኑን ገልጸው፤ ብቃት ያለውና ሁሉንም መመዘኛዎች ያሟሉ ባለሙያዎችን በማግኘት በኩል ክፍተቶች አሉ ነው ያሉት።

እንደ ዶክተር ወርቅነህ ገለጻ፤ በቅርቡ የተደረገው የአምባሰደሮች ሹመት ግልጽ፣ ፍትሃዊና የአገሪቷን የትኩረት አቅጣጫና ብሄራዊ ጥቅም መሰረት ያደረገ ሲሆን በዚህ ረገድ ለውጦች መኖራቸውንም አስረድተዋል።

ብቃት የላቸውን ባለሙያዎች በስልጠና ለማፍራት ጥረት እየተደረገ መሆኑን የገለጹት ሚኒስትሩ፤ በአሁኑ ወቅት በአዲስ መልክ የተመደቡት  በብቃት መስራት ካልቻሉ ከኃላፊነታቸው እንዲነሱ እንደሚደረግም ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ ከባህረ ሰላጤው አገራት ጋር ያላት ግንኙነትም ብሄራዊ ጥቅምን ያስጠበቀ፣ በጥናት ላይ የተመሰረተ፣ ገለልተኛና የማስታረቅ ሚና ያለው መሆኑንም ሚንስትሩ አብራርተዋል።

በሌላ በኩል ከአገር የሸሸ ሀብትን ማስመለስና በድርጊቱ ተሳታፊ የሆኑ አካላትን በህግ እንዲጠየቁ ለማድረግ ተስፋ ሰጪ ጅምሮች መኖራቸውንና ውጤቱ ሲጠናቀቅ ይፋ እንደሚደረግም ገልጸዋል።

ከሱዳን በህገ ወጥ መንገድ መሳሪያ የሚያስገቡ አካላት በቁጥጥር ስር እንዲውሉና ወደ ሱዳን መሳሪያዎችን ከሚልኩ አገራት ጋርም ውይይት በማድረግ በዚህም ለውጥ መኖሩን ገልጸው ችግሩ ሙሉ በሙሉ እስኪወገድም እንሰራለን ነው ያሉት።

ዶክተር ወርቅነህ አክለውም ከኤርትራ ጋር በሚደረገው ስምምነት ላይ በርካታ የህግና ቴክኒክ ስራዎች የሚከናወኑ ሲሆን ድርድሮቹን በሰከነ መንገድና የአገራቱን ነባራዊ ሁኔታ ባገናዘበ መልኩ ተከታታይነት ባለው መልኩ እየተሰራ ነው።

የኢትዮጵያ ድንበር ጉዳይ በተመለከተም በተለይም በበጀት አመቱ ልዩ ትኩረት በመስጠት ቴክኒካል ኮሚቴ ተቋቁሞ  በዕውቀት ላይ የተመሰረተ ስራ እየተሰራ ነው ሲሉም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም