የመጀመሪያው የቮሊቦል ክለቦች የጥሎ ማለፍ ውድድር በጎንደር ከተማ ሊካሄድ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የመጀመሪያው የቮሊቦል ክለቦች የጥሎ ማለፍ ውድድር በጎንደር ከተማ ሊካሄድ ነው
አዲስ አበባ ጥር 21/2011 የመጀመሪያው የቮሊቦል ክለቦች የጥሎ ማለፍ ውድድር በጎንደር ከተማ ከጥር 24 ቀን 2011 ዓ.ም ጀምሮ ሊካሄድ ነው።
በሐበሻ ሲሚንቶ የወንዶች ቮሊቦል ፕሪሚየር ሊግ ላይ የሚሳተፉ ስድስት ክለቦች በውድድሩ ተሳታፊ ይሆናሉ።
የኢትዮጵያ ቮሊቦል ፌዴሬሽን የጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ተክሉ ሸዋዬ ለኢዜአ እንደገለጹት የውድድሩ አላማ የክለቦችን የውድድር አማራጭ ማብዛትና ስፖርቱ ላይ መነቃቃት ለመፍጠር ነው።
ውድድሩ በጎንደር እንዲካሄድ የተደረገው በ1970ዎቹ ከተማዋ ውጤታማ የቮሊቦል ተጫዋቾች ያፈራችና ተጫዋቾቹም ለብሔራዊ ቡድን ተመርጠው በመጫወት ትልቅ ስም ያፈሩ ሲሆን አሁን ግን በከተማዋ ስፖርቱ በመዳከሙ ያንን የማነቃቃት ስራ ለመስራት ነው ብለዋል።
ስፖርቱ በኢትዮጵያ መዘውተር ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ክለቦች የራሳቸው የጥሎ ማለፍ ውድድር እንዳልነበራቸው አስታውሰው የጥሎ ማለፍ ውድድር በክለቦች መካከል ሲካሄድ ለመጀመሪያ ጊዜ እንደሆነም ተናግረዋል።
በውድድሩ ላይ ሙገር ሲሚንቶ በቡሩንዲ በሚካሄደው የምስራቅ አፍሪካ ክለቦች የቮሊቦል ውድድር እንደሚሳተፍ በመግለጽ እንዲሁም አዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ በውስጥ ችግር እንዳማይሳተፉ ለፌዴሬሽኑ ማሳወቃቸውን ነው አቶ ተክሉ ያስረዱት።
በቀጣይም ውድድሩ ተከታታይነት ባለው መልኩ እንደሚካሄድም ጠቁመዋል።
የቮሊቦል ክለቦች የጥሎ ማለፍ ውድድር እስከ ጥር 26 ቀን 2011 ዓ.ም ድረስ ይካሄዳል።
የቮሊቦል ስፖርት ወደ ኢትዮጵያ የገባው አገሪቷ ዘመናዊ ትምህርትን ማስፋፋት ከጀመረችበት ጊዜ አንስቶ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ዘመናዊ ትምህርት ሲጀምር በአብዛኛው በውጭ መምህራን ስለነበር መምህራኑ ስፖርቱንም እንዳስጀመሩት በዘርፉ የተደረጉ ምርምሮች ያሳያሉ።
የስፖርቱ መዘውተር በ1957 ዓ.ም የኢትዮጵያ ቮሊቦል ፌዴሬሽን እንዲመሰረት አስችሏል።
ከ1980ዎቹ በኋላ መጠነኛ መቀዛቀዝ ያሳየው የኢትዮጵያ ቮሊቦል ስፖርት ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ወደ ቀድሞ ደረጃው ለመመለስ በወንድም በሴትም የቮሊቦል ፕሪሚየር ሊግ ማካሄድን ጨምሮ የተለያዩ አበረታች ስራዎች እየተሰሩ ይገኛሉ።