የመከላከያ ሰራዊት ቀን የሰራዊቱንና ህዝቡን ትስስር የበለጠ ለማጠናከር ያስችላል ተባለ - ኢዜአ አማርኛ
የመከላከያ ሰራዊት ቀን የሰራዊቱንና ህዝቡን ትስስር የበለጠ ለማጠናከር ያስችላል ተባለ
አዲስ አበባ ጥር 21/2011 በመጪው ወር የመጀመሪያ ሳምንት የሚከበረው የመከላከያ ሰራዊት ቀን በዜጎችና በሰራዊቱ መካከል ሊኖር የሚገባውን ትስስር ለማጠናከር እንደሚያግዝ የኢትዮጵያ አየር ኃይል አዛዥ አስታወቁ።
በኦሮሚያ ክልል መንግስት እና በኢትዮጵያ አየር ኃይል አዘጋጅነት በአዳማ ከተማ የሚከበረውን 7ኛውን የመከላከያ ሰራዊት ቀን በማስመልከት የአየር ኃይል አዛዡ ብርጋዴር ጀነራል ይልማ መርዳሳ መግለጫ ሰጥተዋል።
በዓሉ ሰራዊቱ የተሰጠውን ህገ-መንግስታዊ ተልእኮ ለመወጣትና የአገሪቱን ሉአላዊነት ለማስጠበቅ የሚያስችል አቅም ያለው መሆኑን ለማሳየትም ዓይነተኛ መንገድ መሆኑንም ብርጋዴር ጀነራል ይልማ በመግለጫቸው ጠቅሰዋል።
በበዓሉ ላይ የሚቀርቡት የተለያዩ ወታደራዊ ትርኢቶችና ትእይንቶች የሰራዊቱን የመፈፀም አቅም ከማሳየት ባሻገር የሰራዊቱን ህዝባዊነት ለማጠናከር የሚያስችል ገፅታ ለመገንባትም ያለው ፋይዳ ከፍተኛ መሆኑን ተናግረዋል።
ከአዳማ ባሻገር ሰራዊቱ በሚገኝባቸው የአገሪቱ ክፍሎች በዓሉ በተለያዩ ትእይንቶች እንደሚከበር ገልፀው፤ ከህዝቡና ከሰራዊቱ አባላት የተውጣጡ አካላት የሚሳተፉባቸውና "በአገር መከላከያ ሰራዊቱ ህዝባዊነትና ግዳጅ አፈፃፀም ላይ ያተኮሩ" የፓናል ውይይቶች ይካሄዳሉ ብለዋል።
ከመጪው የካቲት 2 ቀን 2011 ጀምሮ ለስድሰት ተከታታይ ቀናት የሚቆየውን በዓል በማስመልከት ከሚከናወኑት ሁነቶች መካከል የአየር ኀይልን ጨምሮ የተለያዩ የሰራዊቱ መሰረተ ልማት አውታሮች ጉብኝት፣ የአየር ኃይል ትርኢትና ስፖርታዊ ውድድሮች ይገኙበታል።
ከዚህም ሌላ የደም ልገሳን፣ የፅዳት ዘመቻንና የመሳሰሉትን የሚያካት የተለያዩ የበጎ ተግባር አገልግሎትም በሰራዊቱ አባላት ይከናወናሉ ተብሏል።
የካቲት 7 ቀን 2011 ላይም በዓሉ በአዳማ ስታዲየም ከሁለት ሺህ በላይ ህዝብ በተገኘበት በታላቅ ድምቀት ይጠናቀቃል።