ለዓለም ሰላም መስፈን የሴቶችን የውሳኔ ሰጪነትና ተሳትፎን ማሳደግ ይገባል -ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ

አዲስ አበባ ጥር 20/2011 በዓለም ላይ ሰላምን ለማስፈንና ቀጣይነቱን ለማረጋገጥ የሴቶች ውሳኔ ሰጪነትና ተሳትፎን ማሳደግ እንደሚገባ ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ አሳሰቡ።

''የሴቶችና ሰላምና ደህንነት'' በሚል መሪ ሐሳብ ለሁለት ቀናት የሚቆየው ጉባዔ ዛሬ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን መሰብሰቢያ አዳራሽ ተጀምሯል። 

ጉባዔው በመንግስታቱ ድርጅት የሰላም ማስከበር ተልዕኮ ውስጥም ሆነ በዓለም አቀፍ የፀጥታ መዋቅር ላይ ሴቶች ባላቸው ተሳትፎ ላይ እየመከረ ነው።

የመንግስታቱ ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት ከዛሬ 18 ዓመት በፊት በዓለም ሰላምና ደህንነት ላይ የሴቶች ተሳትፎን አስፈላጊነት በመረዳት ሴቶች በውትድርናና በፀጥታ መዋቅር ውስጥ ያላቸውን የውሳኔ ሰጪነት ተሳትፎ በእጥፍ ለማሳደግ የሚያስችል ግብ አስቀምጦ ነው ሥራ የጀመረው።

በሰላም ማስከበር ተልዕኮ ውስጥ ያለው የሴቶች ተሳትፎ 4 ነጥብ 2 በመቶ ሲሆን እንደ አውሮጳውያን አቆጣጠር በ2020 ቁጥሩን በእጥፍ ለማሳደግ ግብ ቢቀመጥም እስከ አሁን ያለው አፈጻጸም ግን 0 ነጥብ 2 በመቶ ነው።

ዝቅተኛ አፈጻጸም የታየበት አካሄድን ለመለወጥም በቀጣዩ በአሜሪካ ኒውዮርክ በሚካሄደው ጉባዔ ሚኒስትሮች ጠንካራ ውሳኔ ያሳልፋሉ ተብሎም ይጠበቃል።

በጉባዔው መክፈቻ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ እንዳሉት ከዓለም ህዝብ ውስጥ ግማሽ የሚሆኑት ሴቶች በመሆናቸው ተሳትፏቸውን ማሳደግ ካልተቻለ ሰላምን ማረጋገጥ አዳጋች ነው።

ኢትዮጵያ ይህን በመረዳት የሴቶችን ተሳትፎና የውሳኔ ሰጪነት ቁጥርን ለማሳደግ ትኩረት ሰጥታ እየሰራች ሲሆን መንግስት በቅርቡ ከአገሪቷ ርዕሰ ብሔርና መከላከያ ሚኒስትር ጀምሮ ያሉ ትላልቅ የውሳኔ ሰጪነት ቦታ ላይ ሴቶችን መመደቧን አብራርተዋል።

በመንግስታቱ ድርጅት የሰላም ማስከበር ተልዕኮ ላይ ከተሰማሩ 7 ሺህ 500 ኢትዮጵያውያን ወታደሮች ውስጥ 600ዎቹ ሴቶች ሲሆኑ በተልዕኮው ከፍተኛ የሴት ወታደር በማሰማራት ቀዳሚ አገር መሆኗንም ገልጸዋል።

ለዓለም ሰላም መስፈንና ቀጣይነቱን ለማረጋገጥ የሴቶችን ተሳትፎ ማሳደግ ላይ በትኩረት መስራት ይገባል ያሉት ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ኢትዮጵያም የጀመረችውን ስራ አጠናክራ እንደምትቀጥል አረጋግጠዋል።

የመከላከያ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ሌላዓለም ገብረዮሐንስ በበኩላቸው ኢትዮጵያ ከመከላከያ ሠራዊት ጀምሮ በአገሪቷ የፀጥታ ዘርፍ እና የሰላም ማስከበር ተልዕኮ ያላት የሴቶች ተሳትፎ በምሳሌነት የሚጠቀስ ነው ብለዋል።

በአሁንም ወቅት በአገሪቱ በሚካሄደው ለውጥ ውስጥ የሴቶችን ተሳትፎ ለማሳደግና ትላልቅ የውሳኔ ሰጪነት ላይ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ለማድረግ በትኩረት እየተሰራ መሆኑንም ገልጸዋል።

በአገሪቷ በተለያዩ አካባቢዎች የሚከሰቱ ግጭቶችን በቀላሉ ለመቆጣጠር ሴቶች የሚጫወቱት ሚና ከፍተኛ በመሆኑም ተሳትፏቸውን ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

በካናዳ የሰላምና መረጋጋት ፕሮግራም ዋና ዳይሬክተር ላሪሳ ጋላድዛ በበኩላቸው በሴቶች ተሳትፎ ኢትዮጵያ ለዓለም ምሳሌ መሆን የሚችል ነገር እያሳየች ነው ብለዋል። 

ኢትዮጵያ በውስጥና በውጭ በፀጥታና በሌሎች የውሳኔ ሰጪነት ቦታዎች ላይ ሴቶችን በማሳተፍ ዙሪያ ያከናወነችው ተግባር ሌሎች የዓለም አገራት ልምድ መውሰድ እንዳለባቸውም ገልጸዋል። 

ለሁለት ቀናት የሚቆየውን ጉባዔ ኢትዮጵያና ካናዳ በጋራ ያዘጋጁት ሲሆን ከ63 አገራት የተውጣጡ የፀጥታ ዘርፍ ኃላፊዎች ተሳታፊ ናቸው። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም