አገር አቀፍ የቡና ጉንደላ ንቅናቄ ነገ በኦሮሚያ ክልል ይጀመራል - ኢዜአ አማርኛ
አገር አቀፍ የቡና ጉንደላ ንቅናቄ ነገ በኦሮሚያ ክልል ይጀመራል
አዲስ አበባ ጥር 20/2011 አገር አቀፍ የቡና ጉንደላ ንቅናቄ ነገ በኦሮሚያ ክልል እንደሚጀመር የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን አስታወቀ።
በኢትዮጵያ እስካሁን የሚመረተው ቡና በአንድ ሄክታር ከሰባት ኩንታል አልዘለለም።
የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አዱኛ ደበላ ለኢዜአ እንደገለጹት ከ20 ዓመት በላይ ዕድሜ ያላቸው የቡና ተክሎች እያረጁና ምርታማነታቸውም እየቀነሰ በመምጣቱ እንዲጎነደሉና በአዲስ መልክ እንዲያቆጠቁጡ ይደረጋል።
የቡና ጉንደላ ንቅናቄው ነገ በጅማ፣ አጋሮ በደሌና መቱ መካሄድ ይጀምራል።
ንቅናቄው በደቡብ፣ አማራና ሌሎች ክልሎችም በቀጣዩ ሳምንት እንደሚቀጥል ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ ከአንድ ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት በቡና የተሸፈነ ቢሆንም ከዘርፉ አንድ ቢሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሬ እንኳን ማግኘት አልተቻለም።
ይህ ንቅናቄ የቡናን ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ የተያዘው የ15 ዓመት የቡና ስትራቴጂ አካል መሆኑንም ዶክተር አዱኛ ገልጸዋል።
ንቅናቄው ያረጁ ቡናዎችን በመንቀል አዳዲስ ዝርያዎችን በመትከልና በመጎንደል ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ያለመ ነው።
በሽታ የሚቋቋሙና ጥሩ ምርት የሚሰጡ የቡና ዝርያዎችን ከኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ጋር በመሆን እንዲተከሉ የሚደረግ መሆኑንም ዶክተር አዱኛ ገልጸዋል።