ቀጥታ፡

የቀድሞው አፈ-ጉባዔ ዳዊት ዮሃንስ ለዘመናዊ ፓርላማ አሰራርና የዴሞክራሲ ስርዓት መጠናከር ከፍተኛ ሚና ነበራቸው

አዲስ አበባ ጥር 20/2011 የቀድሞው አፈ-ጉባዔ ዳዊት ዮሃንስ ለዘመናዊ ፓርላማ አሰራርና የዴሞክራሲ ስርዓት መጠናከር ከፍተኛ ሚና እንደነበራቸው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ተናገሩ።

የምክር ቤቱ የቀድሞ አፈ-ጉባኤ አቶ ዳዊት ዮሃንስ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል።

አቶ ዳዊት የኢትዮጵያ ህገ-መንግስት ህዳር 29 ቀን 1987 ዓ.ም መጽደቁን ተከትሎ የመጀመሪያው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ በመሆን ከ1988 እስከ 1998 ዓ.ም ድረስ አገልግለዋል።

የቀድሞና የአሁኑ የምክር ቤቱ አባላት አቶ ዳዊት በአፈ-ጉባዔነት የስራ ዘመናቸው ለዘመናዊ ፓርላማ አሰራርና የዴሞክራሲ ስርዓት መጠናከር የነበራቸው አበርክቶ ከፍተኛ እንደነበረ ተናግረዋል።

የምክር ቤቱ አባል ወይዘሮ አማረች ጣሰው በሰጡት አስተያየት አቶ ዳዊት የዴሞክራሲ ምህዳር እንዲሰፋና የህዝቦች ተሳትፎ እንዲጎለብት ጥረት አድርገዋል ይላሉ።

በምክር ቤት አፈ-ጉባዔነታቸው የመጀመሪያው እንደ መሆናቸው ዛሬ ላይ ላለው ዘመናዊ የፓርላማ አሰራር ከፍተኛ አስተዋኦ ያበረከቱ ናቸውም ብለዋል።

ሌላው የምክር ቤቱ አባል አቶ ተሾመ እሸቱም አቶ ዳዊት በአገራችን ስለ ዴሞክራሲ ማውራት በተጀመረበት፣ የህግና የአሰራር ልምድ ክፍተቶች በነበሩበትና የዳበረ አሰራር ባልነበረበት በዚያ ወቅት የአቶ ዳዊት ጠንካራ አመራርነትና በራስ የመተማመን መርሆዎች ለቀጣዮቹ አመራሮች መሰረት ሆነው አገልግለዋል ነው ያሉት።

'እሳቸው ምክር ቤቱን በአፈ-ጉባኤነት የመሩባቸው ወቅቶች ፈተና የነበረባቸው ነበሩ' ያሉት ደግሞ የምክር ቤቱ አባል አቶ ክንፉ ሰይፉ ናቸው።

በምክር ቤቱ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት እንዲጠናከር፣ መርቀቅ ያለባቸው ህጎች እንዲረቀቁ፣ አስፈጻሚው አካል በአግባቡ እንዲከታተልና የቋሚ ኮሚቴ አደረጃጀት የራሱን ስራ በነጻነት እንዲሰራ ለማድረግ ጥረት ማድረጋቸውን አውስተዋል።

አቶ ዳዊት ከስራ ታታሪነታቸው ባሻገር በግል ህይወታቸውም ሁሉን በእኩል ዓይን የሚያዩ፣ ሩህሩህና ለተቸገረ ደራሽ እንደነበሩ በስራ ዘመናቸው አብረዋቸው የሰሩት የምክር ቤቱ አባላት ጨምረው ገልጸዋል።

አቶ ዳዊት በህክምና ሲረዱ ቆይተው ህይወታቸው ማለፉን ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የኢንፎርሜሽን ኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የከፍተኛ ትምህርታቸውን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ በአሜሪካው ጆርጅ ታውንና በኔዘርላንዱ አምስተርዳም ዩኒቨርሲቲዎች ተከታትለዋል።

የጥናት ባለሙያ የሆኑት አቶ ዳዊት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሰላምና ደህንነት ጥናት ተቋም በሰሩበት ጊዜ በደቡብ ሱዳን የሠላም ግንባታ፣ በቻይናና አፍሪካ ግንኙነት፣ በሠላም ማስከበርና በሌሎች ርዕሰ ጉዳዮች ጥናቶች አካሂደዋል።

አቶ ዳዊት ዮሃንስ ባለትዳርና የሶስት ልጆች አባት ነበሩ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም