ቀጥታ፡

የሞጆ ደረቅ ወደብ በ150 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር የማስፋፊያ ግንባታ ሊካሄድ ነው

አዳማ ጥር 20/2011 የኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክ አገልግሎት ድርጅት በ150 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር የሞጆን ደረቅ ወደብ የማስፋፊያ ግንባታ ለማከናወን ዝግጅት ማጠናቀቁን ገለጸ።

በሦስት ዓመት  ውስጥ የሚጠናቀው  የ143 ሄክታር መሬት  የደረቅ ወደብ የማስፋፊያ ግንባታ የደረቅ ወደቡ ኮንተይነሮችን የመያዝ አቅም በ10 እጥፍ ያሳድገዋልም ተብሏል ።

የድርጅቱ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሮባ መገርሳ ለኢዜአ እንደገለጹት የሞጆ ደረቅ ወደብ 80 በመቶ የሚሆነው የሀገሪቷ የወጪና የገቢ ንግድ የሚስተናገድበት ነው።

እየጨመረ የመጣውን የደንበኞች ፍላጎት ማርካት የሚችል ተርሚናል እንዲኖረው የማስፋፊያ ፕሮጀክት ማካሔድ አስፈላጊ ሆኖ መገኘቱን ጠቁመዋል።

አሁን የሀገሪቷ የምጣኔ ሀብት እድገት የደረሰበትን ደረጃ መነሻ በማድረግ ፈጣን የመልቲ ሞዳል አገልግሎት አሰጣጥን ይበልጥ ለማቀላጠፍ ወሳኝ ሚና ያለው የማስፋፊያ ግንባታ መሆኑንም ተናግረዋል።

አቶ ሮባ እንዳሉት የማስፋፊያ ግንባታው የሚከናወነው ከዓለም ባንክ በብድር በተገኘ 150 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ነው።

በአሁኑ ወቅት ግንባታውን ለመጀመር የዲዛይን ሥራ በማጠናቀቅ ጨረታ በማውጣት ላይ መሆናቸውንም አስረድተዋል።

በአሁኑ ወቅት የሞጆ ደረቅ ወደብ ከ14 ሺህ በላይ ኮንቴነሮችን በወጪና ገቢ እያስተናገደ ሲሆን አዲሱ የማስፋፊያ ሥራ ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት ሲጀምር እስከ 150 ሺህ ኮንቴነሮችን የማስተናገድ አቅም ይኖረዋል ተብሏል።

ማስፋፊያው ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ የመልቲ ሞዳል አገልግሎት ለመስጠት ከማስቻሉ ባለፈ በደንበኞች ላይ እርካታን ለማምጣት ጭምር መሆኑን ተናግረዋል።

በዘርፉ የሀገሪቷን ደረጃ ከፍ ማድረግና የባህር ትራንስፖርትና ሎጅስቲክ አገልግሎት አሰጣጥን ዘመናዊነት ለማቀላጠፍ የሚያስችል መሰረተ ልማት ለመዘርጋት ታሳቢ ማድረጉንም ተናግረዋል።

ሀገሪቷ አሁን የደረሰችበትን እድገት መሰረት ያደረገና ቀጣይ ትኩረት ያመላከተ የማስፋፊያ ግንባታ መከናወኑ የወጪና የገቢ እቃዎችን ንግድ ለማቀለጠፍ ሚናው የጎላ መሆኑን የገለጹት ደግሞ በሞጆ ደረቅ ወደብ የትራንዚተሮች አስተባባሪ አቶ ምትኩ አበበ ናቸው።

ፈጣን የመልቲ ሞዳል አገልግሎት መስጠት ለኢኮኖሚ እድገትና መዋቅራዊ ለውጥ ያለው ፋይዳ የላቀ መሆኑን አስረድተዋል።

በአሁኑ ወቅት ደረቅ ወደቡ ብቁ ባለሙያዎችና የተሟላ አገልግሎት መስጠት የሚያስችሉ ማሽነሪዎች በማቅረብ በኩል እየወሰደ ያለው እርምጃ ወቅቱ የሚጠይቀው መሆኑን ጠቅሰው የማስፋፊያ ሥራው ቀጠናዊ የኢኮኖሚ ውህደትን ለማፋጠን ጭምር ያግዛል የሚል እምነት እንዳላቸው ተናግረዋል።

"የመልቲ ሞዳል አገልግሎት አቅም ሲጠናከርና የዘመናዊ ቴክኖሎጂ ባለቤት ስንሆን በቀጠናው ሀገራት ያለን ተፈላጊነት ይጨምራል" ብለዋል።

ይህም ሀገሪቷ ከወጪና ገቢ ንግድ አገልግሎት የምታገኘው የውጭ ምንዛሬ እያደገ በመሄድ በምጣኔ ሀብት እድገት ላይ ጉልህ ሚና መጫወት እንደሚችል አመልክተዋል።

የማስፋፊያ ግንባታው በሦስት ዓመታት ጊዜ ውስጥ ለማጠናቀቅ ዕቅድ መያዙን ከዋና ሥራ አስፈጻሚው ገለጻ ለማወቅ ተችሏል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም