ፋጡማ ሳዶ በኦሳካ ዓለም አቀፍ የሴቶች ማራቶን አሸነፈች

አዲስ አበባ ጥር 20/2011 ኢትዮጵያዊቷ አትሌት ፋጡማ ሳዶ ትናንት በጃፓን በተካሄደው የኦሳካ ዓለም አቀፍ የሴቶች ማራቶን አሸነፈች።

አትሌቷ 2 ሠዓት ከ25 ደቂቃ ከ39 ሴኮንድ በመግባት ሁለተኛውን ምርጥ ሠዓቷንም አስመዝግባለች።

ፋጡማ እ.አ.አ 2015 በካናዳ የቶሮንቶ ማራቶን ያስመዘገበችው 2 ሠዓት ከ24 ደቂቃ ከ16 ሴኮንድ የርቀቱ የግል ምርጥ ሠዓቷ ነው።

"በውጤቱ ደስተኛ ነኝ ነገር ግን ያስመዘገብኩት ሠዓት በቶኪዮ ኦሎምፒክ ውድድር በኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ቡድን ውስጥ ለመካተት በቂ አይደለም" ስትል አትሌቷ ከውድድሩ በኋላ በሰጠችው አስተያየት ገልጻለች።

የ27 ዓመቷ አትሌት ፋጡማ ሳዶ የጎዳና ሩጫ የጀመረችው በ18 ዓመቷ ሲሆን በ10 እና 15 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ሩጫ፣ በግማሽ ማራቶንና በማራቶን ውድድሮች እየተሳተፈች ትገኛለች።

በትናንቱ ውድድር ጃፓናዊቷ አትሌት ሬይ ኦሀራ 2 ሠዓት ከ25 ደቂቃ ከ46 ሴኮንድ፣ ኬንያዊቷ አትሌት ቦርነስ ጄፕኪሩይ 2 ሠዓት ከ26 ደቂቃ ከ1 ሴኮንድ በመግባት ሁለተኛና ሶስተኛ ሆነዋል።

የኦሳካ ዓለም አቀፍ የሴቶች ማራቶን ለ37ኛ ጊዜ የተካሄደ ሲሆን በዓለም አቀፉ አትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማኅበር የወርቅ ደረጃ አለው።

በሌላ በኩል ከትናንት በስቲያ በአሜሪካ ቦስተን በተካሄደ የቤት ውስጥ የአትሌቲክስ ውድድር ሀጎስ ገብረህይወትና ዮሚፍ ቀጄልቻ ድል ቀንቷቸዋል።

በአንድ ማይል /በ1 ነጥብ 6 ኪሎ ሜትር/ ውድድር አትሌት ዮሚፍ ቀጄልቻ 3 ደቂቃ ከ51 ሴኮንድ ከ70 ማይክሮ ሴኮንድ ሲያሸንፍ በዓለም የቤት ውስጥ አትሌቲክስ ውድድር በአንድ ማይል ርቀት 12ኛውን ፈጣን ሠዓት አስመዝግቧል።

በተያዘው የፈረንጆቹ ዓመት የ5 ሺህ ሜትር የወንዶች የዓለም ክብረ ወሰንን ለመስበር ያቀደው አትሌቱ የገባበት ሠዓት በርቀቱ በኢትዮጵያዊ አትሌት የተመዘገበ ፈጣን ሠዓት ሆኗል።

ኬንያዊያኑ ቤትዌል ቢርገን እና ቪንሰንት ኪቤት ሁለተኛና ሶስተኛ ወጥተዋል።

በ3 ሺህ ሜትር ወንዶች አትሌት ሀጎስ ገብረህይወት 7 ደቂቃ ከ37 ሴኮንድ ከ41 ማይክሮ ሴኮንድ በመግባት አሸንፏል።

በዚህ ውድድር ኬንያዊው ኤድዋርድ ቼሴሬክ እና ስፔናዊው አዴል ሜቻል ሁለተኛና ሶስተኛ ደረጃን ይዘዋል።

በ1 ሺህ 500 ሜትር ሴቶች ኢትዮጵያዊቷ ዳዊት ስዩም ሁለተኛ ወጥታለች፤ ካናዳዊቷ ጋብሬላ ስታፎርድ የውድድሩ አሸናፊ ስትሆን አሜሪካዊቷ ኤሊኖር ፑሪየር ሶስተኛ ሆናለች።

የቦስተኑ የቤት ውስጥ የአትሌቲክስ ውድድር የዓለም አቀፉ የአትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማህበር በየዓመቱ ከሚያካሂዳቸው የቤት ውስጥ ውድድሮች አንዱ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም