የኢትዮጵያ አየር መንገድ እስከ 2030 ለማሳካት ያሰበውን እቅድ መተግበር ጀመረ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ አየር መንገድ እስከ 2030 ለማሳካት ያሰበውን እቅድ መተግበር ጀመረ
አዲስ አበባ ጥር 19/2011 የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአውሮፓዊያኑ እስከ 2025 ሊያሳካው ይዞት የነበረውን እቅድ ቀድሞ በማሳካቱ እስከ 2030 ለማሳካት ያሰበውን እቅድ መተግበር መጀመሩን አስታወቀ።
አየር መንገዱ በ74 ሺህ ካሬ ሜትር ላይ ያረፈውን የቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ የማስፋፊያ ግንባታና በ40 ሺህ ካሬ ሜትር ላይ ያስገነባውን ስካይ ላይት ሆቴል ዛሬ አስመርቋል።
የአየር መንገዱ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ተወልደ ገብረማሪያም እንደተናገሩት ከስምንት አመታት በፊት ከአፍሪካ አራተኛ የነበረው የኢትዮጵያ አየር መንገድ በጠንካራ የስራ ውጤት ዛሬ ላይ ከአፍሪካ አንደኛ ደረጃን ይዟል።
በዚህም በአውሮፓዊያኑ አቆጣጠር እስከ 2025 ለማሳካት ይዞት የነበረውን እቅድ ቀድሞ በማጠናቀቁ እስከ 2030 ለመፈፀም የያዘውን እቅድ ማከናወን ጀምሯል ብለዋል።
አየር መንገዱ እስከ 2030 ለማከናወን ከያዛቸው እቅዶች መካከል አቬዬሽኑን የማጠናከር፣ ሆቴልና ቱሪዝም ዘርፍ ላይ መሰማራት፣ የአውሮፕላን ጥገና፣ የሎጀስቲክ አገልግሎትና የኤርፖርት አገልግሎት ስራ መጀመሩን አቶ ተወልደ ገልፀዋል።
"ቪዥን 2025 ቀድመን ስላሳካን አሁን ቪዥን 2030 እየሰራን ነው፤ ቪዥን 2030 አቬሽን ግሩፑ ተጠናክሮ አዳዲስ የቢዝነስ ሴግመንትንስ እየገባን ነው ያለነው ኤርፖርት መገንባት፣ መጠገንና ማስተዳደር እንደ ስራ ዘርፍ ይዘን የሌሎች የአፍሪካ ኤርፖርቶችን ማኔጅ የሚያስደርገን አቅም እንገነባለን አነዚህ ናቸው አዳዲስ ሴግመንቶች"
በአዳዲስ የስራ ዘርፎች ውስጥ የተካተተው የሆቴል ኢንዱስትሪ አላማም የኢትዮጵያን የቱሪዝም ኢንዱስትሪ ለማሳደግ የድርሻውን ለማበርከት መሆኑን ገልፀዋል።
እንደ አቶ ተወልደ ገለፃ በሆቴል ግንባታው ዘርፍ ዛሬ የተመረቀውና 373 ክፍሎች ያሉት ስካይ ላይት ሆቴል የመጀመሪያው ምእራፍ ሲሆን በሁለተኛው ምዕራፍ ደግሞ 630 ክፍሎች ያሉት ታላቅ ሆቴል ለመገንባት ታቅዷል።
የቀድሞው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ግርማ ዋቄ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደገለፁት አየር መንገዱ የያዛቸውን እቅዶች ለማሳካት በተለይ የሰው ሃይል ልማት ላይ አትኩሮ መስራት ይኖርበታል።
"ጊዜ በተቀያየረ ቁጥር የገበያው ሁኔታ ይለወጣል የመንገደኞች ቁጥር ይለወጣል ለዛ የሚያበቃ የአቅም ግንባታ ብዙ መስራት ይጠበቅብናል፣ ወጣቱ ትውልድ ወደ ገበያው እንዲመጣ ብዙ መሰራት አለበት"
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ ዛሬ ሆቴሉን በመረቁበት ወቅት እንደገለፁት የአየር መንገዱ ሰራተኞች የሆቴሉ ድርሻ (ሼር) እንዲኖራቸው መደረጉን አድንቀው ሌሎች ተቋማትም ተሞክሮውን እንዲጋሩት መክረዋል።
ኢዜአ ያነጋገራቸው የአየር መንገዱ ሰራተኞችም ከሆቴሉ ድርሻ እንዲኖራቸው መደረጉ በስራቸው ላይ ተጨማሪ መነሳሳት እንደሚፈጥርላቸው ተናግረዋል።
አየር መንገዱ በ65 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር ያስገነባው ባለ አምስት ኮከብ ሆቴል ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ እና የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋቂ ማሃማት ዛሬ በጋራ መርቀውታል።
ሆቴሉ 373 መኝታዎች እንዲሁም ከሁለት ሺህ በላይ ሰዎችን ማስተናገድ የሚችል አዳራሽም አለው።
የቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ የመንገደኞቸ ማስተናገጃ ተርሚናል የማስፋፊያ ግንባታ ደግሞ የገበያ፣ የመዝናኛና ምግብ ቤቶችና ሌሎች መሰረታዊ አገልግሎት መስጫዎችንም ያካተተ ነው፡፡
በዚህም አሁን ላይ አየር መንገዱ በአመት እያስተናገደ ያለውን 12 ሚሊዮን መንገደኞች ወደ 22 ሚሊዮን ያሳድገዋል ተብሏል።
አየር መንገዱ ከዚህ ቁጥር በላይ መንገደኞችን ማስተናገድ የሚችል ተርሚናል ለመገንባት ከአዲስ አበባ መስተዳደር ጋር እየመከረ መሆኑም ታውቋል።