በምሥራቅ ጎጃም ዞን ለውጡ ሁሉንም የኅብረተሰብ ክፍል ተጠቃሚ ባደረገ መልኩ ይከናወናል - ኢዜአ አማርኛ
በምሥራቅ ጎጃም ዞን ለውጡ ሁሉንም የኅብረተሰብ ክፍል ተጠቃሚ ባደረገ መልኩ ይከናወናል
ደብረ ማርቆስ ጥር 19/2011 በምሥራቅ ጎጃም ዞን የቀድሞውን ሠራዊት አባላት ጨምሮ ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍሎች ተጠቃሚ የሚሆኑበት ለውጥ እንደሚካሄድ የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ ገለጹ።
በዞኑ የቀድሞው የኢትዮጵያ የአገር መከላከያ ሠራዊት አባላት ማህበር ዛሬ በደብረ ማርቆስ ከተማ ተመስርቷል።
ዋና አስተዳዳሪው አቶ አብርሃም አለኽኝ በማህበሩ በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት በአገር ደረጃ የተጀመረው የለውጥ ጉዞ በዞኑም ሁሉንም የኅብረተሰብ ክፍሎች ተጠቃሚ ባደረገ መልኩ ይከናወናል።
"የቀድሞው የኢትዮጵያ የአገር መከላከያ ሠራዊት አባላት የአገራቸውን ሰላም ለማስከበርና የኢትዮጵያን ድንበር ለመጠበቅ መስዋትነት የከፈሉ በመሆናቸው ልናስታውሳቸው ይገባል" ብለዋል።
ለአገር ባለውለታ የሆኑትን የሠራዊቱ አባላትን ከልማቱ ተጠቃሚ ለማድረግም ትኩረት እንደሚሰጥ አመልክተዋል።
በቀጣይም ለመሰረቱት ማህበር ድጋፍ እንደሚደረግ አቶ አብርሃም አስታውቀዋል።
አባላቱ ለመደራጀት ያቀረቡትን ጥያቄ ለመመለስ እስካሁን ድጋፍ ሲደረግ እንደነበርም በማስታወስ።
የማህበሩ ሊቀመንበር የመቶ አለቃ ሙሉአለም አበበ አባላቱ ለአገር በከፈሉት መስዋዕትነት ልክ ተጠቃሚ ካለመሆናቸውም በላይ፤ ተጽዕኖ ሲደረግባቸው መቆየቱንም ይናገራሉ።
እንደ አገር የተጀመረውን ለውጥ ተከትሎ በማህበር ለመደረጃት በመብቃታቸውም መደሰታቸውን ገልጸዋል።
"'የደርግ ሠራዊት' በመባል ይሰጠን የነበረውን ጸረ ልማት ስማችን ተቀይሮ ክብራችንና ለአገር ተቆርቋሪ መሆናችን እንዲታወስልንና አቅማችን በፈቀደ መልኩ በአገራዊ ለውጡ ለመሳተፍ ማህበሩን ማቋቋም አስፈልጓል" ብለዋል።
ከማህበሩ አባላት መካከል መቶ አለቃ ፈረደ ተስፋው ማህበሩ እሳቸውም ሆነ የሙያ ባልደረቦቻቸው ለአገር ሰላም፣ አንድነትና ሉዓላዊነት ያበረከቱትን አስተዋጽኦ ለሕዝብ ለማሳወቅ እንደሚሰራ አስረድተዋል።
በማህበሩ መሥራች ጉባዔ በዞኑ 21 ወረዳዎች የሚገኙ ከ4 ሺህ በላይ የቀድሞ የአገር መከላከያ ሠራዊት አባላት ተገኝተዋል።