የጅማ ከተማን ጥንት ወደ ምትታወቅበት የንግድ እንቅስቃሴ ለመመለስ የንግዱ ማህበረሰብ አስተዋጽኦ ተጠየቀ - ኢዜአ አማርኛ
የጅማ ከተማን ጥንት ወደ ምትታወቅበት የንግድ እንቅስቃሴ ለመመለስ የንግዱ ማህበረሰብ አስተዋጽኦ ተጠየቀ
ጅማ ጥር 19/2011 ጅማ ከተማን ጥንት ወደምትታወቅበት የንግድ እንቅስቃሴ ለመመለስ የንግድ ማህበረሰቡ ሚናውን እንዲወጣ ተጠየቀ።
የጅማና አካበቢዋ የንግድ ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት 50ኛ ዓመት የወርቅ ኢዮቤልዩ ክብረ በዓልን አስመልክቶ የውይይት መድረክ አካሂዷል።
በውይይቱ የጅማ ከተማ ከንቲባ አቶ መኪዩ መሐመድ በዚሁ ወቅት እንደተናገሩ ከተማዋ አሁን ላለችበት የዕድገት ደረጃ የደረሰችው በአባጅፋር ዘመነ መንግስት ለነጋዴዎችና ለንግዱ ማህበረሰብ ምቹ ሁኔታ በመፈጠሩ እንደነበር አስታውሰዋል።
ያኔ ጅማ የንግድ ቀለበት ሆና የራሷን ሽቀጦች ወደ ውጭ የምትልክባቸውና የምታስገባባቸው እንደ ሰንሰለት የተሳሰሩና በየአቅጣጫው የተዘረጉ መስመሮች እንደነበራትም አንስተዋል፡፡
ለአብነትም የንግድ መስመሩ መነሻውን ቦንጋ አድርጎ የነጋዴዎች ማረፊያ ጅማ ጅሬን ላይ ሲሆን መስመሮቹም ምፅዋ፣ዘይላና ታጁራ ያካትቱ እንደነበር ጠቁመዋል።
ከተለያዩ አካባቢዎች ወደ ከተማዋ የሚመጡ ነጋዴዎች ምጣኔ ሀብቷ በማሳደግ ረገድ የነበራቸውን ሚና የዚህ ዘመን ነጋዴዎች ለመመለስ ጥረት እንዲያደርጉ ጠይቀዋል ።
የጅማ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ፕሬዚዳንት አቶ ሰብስብ አባፊራ በበኩላቸው "50ኛ አመት የወርቅ ኢዮቤልዮ በዓል የጅማ ከተማን ንግድ የምናዘምንበትና ወደ ቀድሞ ታሪኳ ለመመለስ የምንስራበት በዓል ይሆናል" ብለዋል ።
ምክር ቤቱ የንግድ ማሰልጣኛ ተቋም ገንብቶ ግብዓቶችን በማሟላት ላይ እንደሚገኝ አመልክተዋል።
የከተማዋ ንግድ ማሳደግ ለከተማዋ ዕድገትና ለውጥ የሚኖረው ፋይዳ ከፍተኛ መሆኑን የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ዋና ጸሐፊ አቶ ውቤ መንግሥቱ አስታውቀዋል ።
የንግድ ማህበረሰቡ ወሳኝ በመሆኑ ሁሉም ለሰላም ዘብ መቆም እንደሚገባው አሳስበዋል።
የንግዱ ማህበረሰብ ያለፈውን ጠንካራ የንግድ ታሪክ ከተማዋ ወደ ነበረችበት መልካም ታሪክ ለመመለስ መሥራት እንደሚገባ በመድረኩ ላይ የተሳተፉት አቶ ጀማል አህመድ ተናግረዋል።
የጅማና አካባቢዋ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት 12 ሺህ አባላት ያሉት መሆኑ ከምክር ቤቱ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።