ቀጥታ፡

የላልይበላን ጥገናና ዘላቂ ልማት የሚከውነው የፈረንሳይ የቴክኒክ ቡድን የማኅበረሰቡን ይሁንታ ጠየቀ

አዲስ አበባ ጥር19/2011 ከፍተኛ ስጋት የተደቀነበትን የቅዱስ ላልይበላ አብያተ ክርስቲያናት ጥገናና ዘላቂ ልማት ለማከናወን የተስማማው የፈረንሳይ የቴክኒክ ቡድን የማህበረሰቡ የይሁንታ ማረጋገጫ እንዲሰጠው ጠየቀ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በፈረንሳይ ቆይታቸው የላልይበላን ቅርስ ጥገናና ዘላቂ ልማት አስመልክቶ ከአገሪቱ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ጋር ባደረጉት ውይይት ድጋፍ መጠየቃቸው ይታወቃል።

ባለሙያዎቹ የጥናቶቹን መነሻዎች በመያዝ በስፍራው ተገኝተው ምልከታ በማድረግና የራሳቸውን እይታ በማካተት መደረግ አለበት ያሉትን ሃሳብ ማቅረባቸውንና ስምምነት ላይ መደረሱን የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ገዛኸኝ አባተ ለኢዜአ ገልጸዋል።

"የፈረንሳይ ቴክኒክ ቡድን በኮንስትራክሽን ዲዛይንና ሱፐርቪዥን ስራዎች ኮርፖሬሽን ያቀረበው የፍኖተ ካርታ ከእነሱ ጥናትጋ በቀጥታ እንደሚገናኝ፣ አንድ ቅርስ ሲጠገን እንዲህ አይነት አሰራር መከተል እንዳለባቸውና ከእነሱም ጋር የተያያዘ ስራው ተለያይቶ ቢሰራም የእነሱን መንገድ የተከተለና ለቅርስ ጥገናው ጥሩ ግንዛቤና ጥሩ ጅምሮች እንዳሉ ስምምነት ላይ ተደርሷል። ሙሉ በሙሉ ተቀብለውታል ፍኖተ ካርታውን ሁለተኛው ትናንት ለማስጀመር የማህበረሰቡን ይሁንታ እንደሚፈልጉ ማህበረሰቡ እንዲያምንበት ለማንኛውም ህብረተሰብ ክፍል የጥገናው ሂደት በሚገባቸው ቋንቋ ተተርጉሞ ግልጽ የሆነ ውይይት ተደርጎ የማሳመን ስራ ተሰርቶ ሁሉም አካል አጋር እንዲሆን ከጎናቸው እንዲቆም እንደሚፈልጉ ተነግሯል።"

የቅርሱን ሁኔታና እስካሁን የተከናወኑ ተግባራትን በተመለከተ የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለስልጣን ሪፖርት አቅርቧል።

በተመሳሳይ የፈረንሳዩ የባለሙያዎች ቡድን የጥናት ውጤቱን አቅርቦ ውይይት ተደርጎበታል።

መጠለያዎቹን በተመለከተ መነሳታቸው ተገቢ ቢሆንም አሁን ባለው ሁኔታ ጥገና ሳይደረግ መነሳቱ የበለጠ አደጋ ስለሚኖረው ጥገና እየተደረገ የሚነሱ ይሆናል ተብሏል።

ባለሞያዎቹ ካላቸው ልምድ ተነስተው ችግሩን በዘላቂነት የሚፈታ ስራ በጥንቃቄ ለመከወን መስማማታቸውንም አቶ ገዛኽኝ ተናግረዋል።

"ፈረንሳይ እንደሚታወቀው በዓለም በቅርስ ጥገና፣ በቅርስ እንክብካቤ፣ ልማት ላይ ከፍተኛ የሆነ ልምድ አላቸው፤ እነዚህ አጥኚዎች በአንድም በሌላም እነዚህን አገር ውስጥ ያሉትን ቅርሶች ጨምሮ የሌሎች አገር ቅርሶች ከሙያ ስነ-ምግባራቸው በመነሳት ጥናቶች የሚያጠኑ ሰዎች ናቸው። ቅዱስ ላሊበላንም በተደጋጋሚ ጊዜ ያጠኑ መሆናቸው ተረጋግጧል። የፈረንሳይ መንግስት ካለው ልምድ አንፃር ይሰራል ተብሎ የታመነበት ስለሆነ አሁንም ያቀረቡት ጥናት በሙሉ ፈቃደኝነት የኢትዮጵያን ህዝብ ጥያቄ፣ የመንግስትን ጥያቄ ለመፍታት በባለቤትነት ስሜት በአጭር ጊዜ ውስጥ ይሄን መልስ የሰጡ ከመሆናቸው ጋር ተያይዞ ጥሩ ልምድ አላቸው ብለን እናስባለን።"

የኮንስትራክሽን ዲዛይንና ሱፐርቪዥን ሥራዎች ኮርፖሬሽንም የቅርሱን አጠቃላይ ሂደትና የስታንዳርድ ሁኔታ አስመልክቶ የተዘጋጀውን ፍኖተ ካርታ ማቅረቡንም አቶ ገዛኽኝ ገልጸዋል።

"በመንግስት የተቋቋመው የኮንስትራክሽን ዲዛይንና ሱፐርቪዥን ስራዎች ኮርፖሬሽን ይሄንን ኃላፊነት ሰጥቶ የወጣው ፍኖተ ካርታ በእኛም በኩል ያለውን ልምድ ወይም ስታንዳርድ በእነሱ በኩልም በተመሳሳይ መንገድ መምጣቱ የተናበበ ፍላጎት፣ የተናበበ ጥናት፣ አንድ አይነት የሆነ ውሳኔ መወሰኑ ፕሮጀክቱን ውጤታማ ያደርገዋል፤ ከችግርም ቢሆን ባለሙያዎቻችን የተማሩት ነገር አለ።"

ስራው በኢትዮጵያዊያንና ፈረንሳዊያን ባለሙያዎች በቅንጅት የሚሰራ ሲሆን የፕሮጀክቱን ሙሉ ወጪ የፈረንሳይ መንግስት እንደሚሸፍን ገልጸዋል።

ፕሮጀክቱ ሁሉን አቀፍ ምላሽ የያዘ ጥገና፣ ስልጠና፣ የእውቀት ሽግግር እንዲሁም የአካባቢውን ልማት፣ የቤተ-መጻህፍትና የሙዚየም ስራዎችን ያካትታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም