በአፋር ክልል በኢንቨስትመንት ዘርፍ የተሰማሩ ባለሃብቶች ውጤታማ መሆን ጀምረዋል

ሰመራ ግንቦት19/2010 የአፋር ክልሉ አቶ አህመድ ሃጂ ዋሴ በኢትዮጵያ ወታደራዊው አገዛዝ ወድቆ አዲስ የፖለቲካዊና ምጣኔ ኃብታዊ ስርዓት ተግባራዊ በሆነባቸው ያለፉት 27 ዓመታት አገሪቱ ካፈራቻቸው አያሌ ባለኃብቶች መካከል አንዱ ናቸው። እኚህ ሰው የዛሬ 27 ዓመት በትምህርታቸው በመግፋት ህይወታቸውን የማሻሻል ታላቅ ተስፋ በውስጣቸው የሚዋልል ታዳጊ ወጣት በነበሩበት በዚህ ወቅት ግን አገሪቱ ጦርነትን ጨምሮ በተለያዩ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ተተብትባ ስለነበር የሚታያቸው ለውጥ አልነበረም። "በወቅቱ አገራዊ የስርዓት ለውጥ ባይመጣ ኖሮ አሁን ለደረስኩበት ደረጃም ሆነ ስለ እኔ ማንነት ማውራት አንችልም ነበር" ይላሉ ከ27 ዓመት በፊት በጨለመ ተስፋ ውስጥ የነበሩት የቀድሞ ተማሪ የአሁኑ ሚሊየነር አቶ አህመድ ሃጂ ዋሴ። አቶ አህመድ ትውልዳቸውም ሆነ እድገታቸው በአፋር ክልል ሲሆን ከ27 ዓመት በፊት በክልሉ ያሉት ትምህርት ቤቶች በጣት የሚቆጠሩና ለሁሉም ተደራሽ እንዳልነበሩ ያስታውሳሉ። "በወቅቱ እንደ እድል ሆኖ ቤተሰቦቼ በከተማ ስለሚኖሩ ትምህርት ቤት የመግባት እድል ገጥሞኝ 6ኛ ክፍል ደርሼ ነበር" ያሉት አቶ አህመድ በወቅቱ በነበረው ተጨባጭ ሁኔታ ትምህርት የመማር እድላቸው አጣብቂኝ ውስጥ ገብቶ እንደነበር ይናገራሉ። "የደርግ ስርዓት ወድቆ ህዝባዊ መንግስት ባይመሰረት ኖሮ እኔም ትምህርቴን አቋርጬ ብሄራዊ ውትድርና ወይም እንደ ብዙ ጓደኞቼ የእንሰሳትን ጭራ እየተከተልኩ ህይወቴን ስገፋ ልታገኙኝ ትችሉ ነበር" በማለት ወቅቱ ፈጥሮባቸው የነበረውን ስጋት ያብራራሉ። ባለኃብቱ እንደሚሉት በአሁኑ ወቅት የአፋር ክልልን ነባራዊ የአኗኗር ሁኔታ ያገናዘቡ በርካታ አገልግሎቶች በመስፋፋት ላይ ናቸው፤ ይህ ደግሞ በክልሉ ምጣኔ ኃብታዊ እድገት ላይ ትልቅ ሚና እየተጫወተ ነው። አቶ አህመድ በአሁኑ ወቅት 70 ሚሊዮን ብር በሚጠጋ መዋእለ ንዋይ በትምህርት፣ በጨው ንግድና በኮንስትራክሽኑ ዘርፍ ተሳትፈው ለክልሉ ብሎም ለአገር እድገት የበኩላቸውን ሚና በመጫወት ላይ ናቸው። ሆቴልና ሆስፒታል የመገንባት እቅድ እንዳላቸውም ባለኃብቱ ይገልፃሉ። በተሰማሩባቸው የኢንቨስትመንት መስክ አማካኝነት ለሁለት መቶ ቋሚ ሰራተኞችና በየወሩ ደግሞ እስከ አራት መቶ ለሚደርሱ ዜጎች የሥራ  እድል መፍጠራቸውን ይናገራሉ። መንግስት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ለክልሉ ኢንቨስተሮች የሚያደርገው ድጋፍ እያስመዘገቡት ላለው እድገት ትልቅ አስተዋጽኦ ማበርከቱ አቶ አህመድ ይናገራሉ። ክልሉ ለኢንቨስትመንት በሰጠው ትልቅ ትኩረት ምክንያት በርካታ ባለኃብቶችን መሳብ እንደተቻለ የሚገልፁት ደግሞ የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አወል አርባ ናቸው። 'ኢንቨስትመንት ሲታሰብ ለማህበረሰቡ ጥቅም የቆመ መሆኑን በቅድሚያ ማረጋገጥ ያስፈልጋል' ያሉት አቶ አወል ለባለኃብቱም ሆነ ለማህበረሰቡ ትልቅ ዋስትና በሚሆን መልኩ ቦታዎችን በመለየት ወደ ስራ መገባቱን ገልጸዋል። በኢንቨስትመንት መስክ የተሰሩ ስራዎች ውጤት በማሳየት ላይ መሆናቸውን የሚናገሩት ምክትል ርእሰ መስተዳድሩ፤ በክልሉ ርዕሰ መዲና ሰመራ የሆቴል ልማት ባለሃብቶችን በማሳተፍ በተደረገው እንቀስቃሴ ባጭር በርካታ ሆቴሎች ተገንብተው ወደስራ መግባታቸውን ጠቁመዋል። ኢንቨስትመንቱ ዘንድሮ በክልሉ አስተናጋጅነት የተከበረውን የብሄር ብሄረሰቦችን በዓል ያለ ምንም ችግር ለማስተናገድ መቻሉን ገልጸዋል። ክልሉ በርካታ የኢንቨስትመንት እድሎች ያሉበት ሲሆን ማእድን ልማትና በቱሪስት ሰፊ እምቅ ሐብት አለው።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም