የኢትዮጵያ አየር መንገድ የአቪዬሽን ዩኒቨርሲቲ መገንባት አለበት - ጠ/ሚ አብይ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ አየር መንገድ የአቪዬሽን ዩኒቨርሲቲ መገንባት አለበት - ጠ/ሚ አብይ
አዲስ አበባ ጥር 19/2011 አየር መንገዱ በአፍሪካ ብርቅዬ አየር መንገድ መሆን እንዲችል የአቪዬሽን ዩኒቨርሲቲ በመገንባት 'ባለሙያዎችን ማፍራት አለበት' ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ ተናገሩ።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ በ1 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር ያስገነባው ስካይ ላይት ሆቴል ለምረቃ በቅቷል።
በተመሳሳይ 345 ሚሊዮን ዶላር ወጪ የሆነበት የመንገደኞች ማስተናገጃ ተርሚናል ማስፋፊያ ፕሮጀክትም ተመርቋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ በምረቃ ስነ ስርዓቱ ላይ ባደረጉት ንግግር በእስካሁኑ ሂደት በአቪዬሽን ኮሌጅ ለአብራሪዎች፣ የበረራ አስተናጋጆችና ቴክኒሻኖች ስልጠና እየተሰጠ ያለ ቢሆንም በቀጣይ አየር መንገዱ እንደስሙ የአፍሪካ ብርቅዬ ለመሆን ዩኒቨርሲቲ እንደሚያስፈልገው ተናግረዋል።
ዩኒቨርሲቲው የሚያስተምር፣ ዲዛይኖችን የሚያለማምድና በርካታ ሙያተኞችን የሚያፈራ መሆን እንዳለበትም ተናግረዋል።
አየር መንገዱ የአገር ውስጥና የውጭ ባለሃብቶችን በማሳተፍ ብቁ ባለሙያዎችን የሚያፈራና 'ለአፍሪካ ብሎም ለኢትዮጵያ ብርቅዬ የሆነ ዩኒቨርሲቲ በቅርቡ እንደሚገነባ ተስፋ አለኝ' ብለዋል።
የአየር መንገዱ የመንገደኞች ማስተናገጃ ተርሚናል አቅሙንም ከፍ ማድረግ እንዳለበትም ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያሳሰቡት።
የመንገደኞች ማስተናገጃ ተርሚናሉ የማስፋፊያ ፕሮጀክት በዓመት 22 ሚሊዮን ተሳፋሪዎችን ማስተናገድ የሚያስችል ነው።
100 ሚሊዮን ህዝብ ላላት አገር የተርሚናሉ አቅም አነስተኛ በመሆኑ አየር መንገዱ የተርሚናሉን የማስተናገድ አቅም 100 ሚሊዮን ተሳፋሪዎች ማስተናገድ ወደሚችልበት ማሳደግ እንዳለበትም ዶክተር አብይ ተናግረዋል።
የአየር መንገዱ ሰራተኞችና የማኔጅመንት አባላት ላበረከቱት አስተዋፅኦ ምስጋና ያቀረቡት ዶክተር ዐብይ መንግስት ከጎናችሁ በመሆን 'የላቀ ስማችሁ ከፍ እንዲል ይሰራል' ብለዋል።
"የኢትዮጵያን አየር መንገድ ኩሩና ስመ ገናና ያደረገው የመደመር ፍልስፍና ነው" ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጠንካራ ራዕይ፣ የስልጠና ማዕከል፣ አብራሪና አስተናጋጆች እና የቴክኒክ ሙያተኞችና ሰራተኞች ባይኖሩት አሁን ያለውን ስምና ዝና ሊይዝ አይችልም ነበር ብለዋል።
"በቀጣይም ሴት ወንድ፣ ኦሮሞ አማራ፣ እስላም ክርስቲያን፣ ሳንል በመደመር እንዲህ የሚያምር ስራ እየሰራን በአፍሪካ ስማችንን ማግነን ቀዳሚ ተግባራችንና እምነታችን ሊሆን ይገባል" ነው ያሉት።
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አየር መንገዱ በገነባው ሆቴል ሰራተኞቹ ተቀጣሪ ብቻ ሳይሆኑ ባለቤት ጭምር እንዲሆኑ መጋበዙ የሰራተኞችን ትጋት የሚጨምር በመሆኑ ሌሎች ድርጅቶችም ትምህርት የሚወስዱበት እንደሚሆን እምነት እንዳላቸው ገልፀዋል።