ቀጥታ፡

ጎዳና ተዳዳሪነትን ከምንጩ ለመቀነስ ማኅበረሰቡን እናስተምራለን - የሃይማኖት አባቶችና አርቲስቶች

አዲስ አበባ ጥር 19/2011 የጎዳና ተዳዳሪነትን ከምንጩ ለመቀነስ ማኅበረሰቡ ላይ ትልቅ የግንዛቤ ስራ መስራት እንደሚጠበቅባቸው የኪነ ጥበብ ባለሙያዎችና የሃይማኖት አባቶች ተናገሩ።

ለጎዳና ተዳዳሪነት አጋላጭ ምክንያቶች ላይ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ የግንዛቤ ስራ እየተሰራ ቢሆንም በቂ አለመሆኑን ገልጸዋል።

አርቲስቶችና የሃይማኖት አባቶቹ በተለይ ህፃናትን ለጎዳና እያደረጉ ያሉትን በቤተሰብ ውስጥ የሚፈጠሩ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውሶች ለማቃለል እንደሚሰሩ ተናግረዋል።

ጽምጻዊት ሃመልማል አባተ ጥበብ የማህበረሰቡ ህይወት ነፀብራቅ እንደመሆኑ ለጎዳና ተዳዳሪነት የሚያጋልጡ እንደ ኤች.አይ.ቪና የቤተሰብ መፍረስ ችግሮች ላይ ከማስተማር አኳያ 'ብዙ መስራት ይጠበቅብናል' ብላለች።

በፊልም፣ በሙዚቃና በቲያትር ስራዎች ለህብረተሰቡ ስለ ጎዳና ህይወት አስከፊነትና አጋላጭ ማህበራዊ ቀውሶችን በማሳየት የማስተማር ትልቅ ሚና ከባለሙያዎች የሚጠበቅ እንደሆነም አክላለች።

ድምፃዊ ሃጫሉ ሁንዴሳ በበኩሉ ከማስተማሩ ጎን ለጎን በተለያዩ መድረኮች ለበጎ ፈቃድ የሚውሉ መድረኮችን በማዘጋጀት 'የዜግነት ሃላፊነታችንን መወጣት ይኖርብናል' ሲል ገልጿል።

የሚሰባሰበው ገንዘብ ለታለመለት ዓላማ መዋሉን መከታተል እንደሚያስፈልግና ጎዳና የወጡ ዜጎችን መጠየቅና ችግራቸውን መካፈል እንደሚገባም ገልጿል።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን የዓለም አቀፍ ግንኙነት የበላይ ኃላፊ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ ዶክተር አቡነ አረጋዊ በበኩላቸው ቤተ ክርስቲያን ስለ ጋብቻ፣ ስነ-ምግባርና የተለያዩ ማህበራዊ ትስስሮች ስትሰጥ የቆየችውን ትምህርት አጠናክራ ትቀጥላለች ነው ያሉት።

'የጎዳና ተዳዳሪነትን ለመቀነስ በየተቋማቱ ከምንሰጠው የሃይማኖት ትምህርት ባሻገር ከመንግስትና መንግስታዊ ካልሆኑ ተቋማት ጋር በቅንጅት መስራት ይኖርብናል' ያሉት ደግሞ የሰላም መስጂድ ኢማም ሰኢድ ዓሊ ናቸው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም