የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ችግረኞችን በዘላቂነት ማቋቋም የሚያስችል ትረስት ፈንድ ይፋ አደረገ - ኢዜአ አማርኛ
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ችግረኞችን በዘላቂነት ማቋቋም የሚያስችል ትረስት ፈንድ ይፋ አደረገ
አዲስ አበባ ጥር 19/2011 የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች የተዳረጉ ዜጎችን በዘላቂነት ማቋቋም የሚያስችል የማህበራዊ ትረስት ፈንድ ይፋ አደረገ፡፡
ትረስት ፈንዱ የጎዳና ተዳዳሪዎችን፣ ጧሪ ያጡ አረጋዊያንን፣ ወላጆቻቸውን ያጡ ህፃናትን፣ የአካል ጉዳተኞችን እንዲሁም ለተለያዩ ማህበራዊ ችግሮች የተዳረጉ ዜጎችን በዘላቂነት ለማቋቋም ያግዛል ተብሏል።
ፈንዱ ይፋ ሲደረግ የኢፌዲሪ ፕሬዘዳንት ሳህለ ወርቅ ዘውዴን ጨምሮ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማ፣ የሃይማኖት አባቶች፣ አርቲስቶች ፣ አትሌቶችና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።
ፕሬዘዳንቷ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት "አዲሲቷን ኢትዮጵያ እንገነባለን ስንል ሁሉንም ልጆቿን ይዘን በመሆኑ ሁላችንም የተቸገሩትን የመደገፍና የማገዝ አገራዊ ሃላፊነት አለብን" ብለዋል።
በመሆኑም የተቸገሩና ወደ ጎዳና የወጡ ዜጎችን በቀጣይ በዘላቂነት ችግራቸውን ለመፍታት የጋራ ጥረት መደረግ እንዳለበትም ተናግረዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማ በበኩላቸው የመንግስትና የግል ተቋማትን ጨምሮ ማንኛውም ዜጋ ሃላፊነት ወስዶ ወገኖቹን እንዲያግዝ በማለት ጥሪያቸውን አቅርበዋል።
በአስተዳደሩ በኩል ለትረስት ፈንዱ ማቋቋሚያነት የሚያግዝ 100 ሚሊዮን ብር መመደቡን የገለፁት ምክትል ከንቲባው የኢትዮጵያ አየር መንገድም አንድ ትኬት ሲቆረጥ አንድ ብር ገቢ ለማድረግ ቃል ገብቷል ብለዋል።
አርቲት ቴድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ) ደግሞ አንድ ኮንሰርት በማዘጋጀት ገቢውን በሙሉ ለዚሁ ትረስት ፈንድ ገቢ ለማድረግ ቃል መግባቱን ተናግረዋል።
ለትረስት ፈንዱ የገንዘብ ማሰባሰቢያ አማራጭ እንዲሆንም አጭር የፅሁፍ መልዕክት መላኪያ 6400 ይፋ ተደርጓል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የማህበራዊ ትረስት ፈንድ ማቋቋሚያ ደንብ ቁጥር 106/2011 ተብሎ ይጠቀሳል።