ድሬዳዋ ወደ ቀደመ ሰላሟ እየተመለሰች ነው - ኢዜአ አማርኛ
ድሬዳዋ ወደ ቀደመ ሰላሟ እየተመለሰች ነው

ድሬዳዋ ጥር 18/2011 ድሬዳዋ ከተማ ወደ መረጋጋት እየተመለሰች በመሆኑ መደበኛ የስራ እንቅስቃሴው ወደ ነበረበት መመለሱን የከተማው ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ።
በመከላከያ ሰራዊት፣በሌሎች የጸጥታ ኃይሎችና በህዝቡ ጥረት እየመጣ ያለውን ሰላም ለማስጠበቅ የምስራቅ ዕዝ መከላከያ ሠራዊት ወስዶ እየሰራ ይገኛል።
የከተማው ፖሊስ ኮሚሽን ህዝብ ግንኙነት ዲቪዥን ኃላፊ ዋና ሳጅን ባንተአለም ግርማ እንደተናገሩት፤ ባለፉት አራት ቀናት ወጣቶች ሲያካሄዱት የነበረው የተቃውሞ ሰልፍና እሱን ተከትሎ የተከሰተው አለመረጋጋት ዛሬ ቆሟል፡፡
ግርግሩን ተከትሎ በመንግስታዊና በግለሰብ ተቋማት ላይ መጠነኛ ጉዳት መድረሱን ገልጸው በችግሩ መፈጠርና መባባስ የተጠረጠሩ ቀደም ሲል የተያዙትን ጨምሮ ሁለት መቶ ሰዎች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን ተናግረዋል።
በዛሬው ዕለት ለተፈጠረው አንጻራዊ ሰላምና መረጋጋት ወጣቱ ላሳየው ተሳትፎ ዋና ሳጅን ባንተአለም በኮሚሽኑ ስም አመስግነው በወጣቱ ጥያቄዎች ሰበብ ድብቅ አጀንዳዎችን የሚያራምዱ አካላትን ለህግ ለማቅረብ የጀመሩትን ጥረት እንዲቀጥሉ ጠይቀዋል።
የድሬዳዋ አስተዳደር መንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ አቶ እስቂያስ ታፈሰ በበኩላቸው እንደተናገሩት ምስራቅ ዕዝ መከላከያ ሠራዊት በከተማው ሰላምን የመጠበቅና የህግ የበላይነትን የማረጋገጥ ኃላፊነትን በበላይነት ተረክቦ እየሰራ ይገኛል፡፡
በአሁኑ ሰዓት በተፈጠረው መረጋጋት መደበኛ እንቅስቃሴ በከተማው እየተከናወነ መሆኑን ገልፀው በቀጣይ የወጣቶቹን መሰረታዊ ጥያቄዎች መፍታት የሚያስችሉ ውይይቶች እንደሚደረጉ ተናግረዋል፡፡
በከተማው ሰላምና መረጋጋት መፈጠሩ ቢረጋገጥም ዛሬ በመልካ ጀብዱ ቀበሌ መጠነኛ ግጭት መታየቱን የቀበሌው ነዋሪዎች ለኢዜአ ሪፖርተር ገልፀዋል።