ቀጥታ፡

ህገ ወጥ የሐዋላና የገንዘብ ዝውውርን ለማስቆም በቂ የፖለቲካ ቁርጠኝነት የለም.. የፋይናንስ ደህንነት መረጃ ማዕከል

አዲስ አበባ ጥር 18/2011 በኢትዮጵያ ህገ ወጥ የሐዋላና የገንዘብ ዝውውርን ለማስቆም በቂ የፖለቲካ ቁርጠኝነት እንደሌለ የፋይናንስ ደህንነት መረጃ ማዕከል አስታወቀ።

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ለመጀመሪያ ጊዜ የማዕከሉን የስራ እንቅስቃሴ ዛሬ የመስክ ምልከታ አድርጓል።

የማዕከሉ ዋና ዳይሬክተር አቶ ኪዳነማርያም ገብረጻዲቅ ለቋሚ ኮሚቴው ባደረጉት ገለጻ፤ በኢትዮጵያ የፋይናንስ ስርዓት ላይ አደጋ ሊሆኑ የሚችሉ ህገ ወጥ የሐዋላና የገንዘብ ዝውውርን ለመከላከል ማዕከሉ አስፈላጊውን ጥረት ቢያደርግም ከአስፈጻሚው አካል በቂ የፖለቲካ ቁርጠኝነት የለም።

''ማዕከሉ በ2007 ዓ.ም ከፌዴራል ፖሊስና ከየመረጃ መረብ ደህንነት ኤጀንሲ ጋር በመተባበር ባካሄደው ጥናት በአገሪቱ የፋይናንስ ስርዓት ውስጥ ህገ ወጥ የሐዋላና የገንዘብ ዝውውር መሠረታዊ ችግሮች እንደሆኑ ተረጋግጧል'' ብለዋል።

በተለይም የውጭ አገር ገንዘብን የማስወጣትና የማስገባት ጉዳይ በአዲስ አበባ በስፋት የሚታይ ሲሆን በህገ ወጥ ተግባሩ ላይ ከሰተማሩ አካላት ውስጥ ነጋዴዎችና የመንግስት ባንክ የስራ ኃላፊዎች እንዳሉበትም ዋና ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል።

እንደ አቶ ኪዳነማርያም ገለጻ፤ በኢትዮጵያ የውጭ ሐዋላ ፍሰት መደበኛ ባልሆነ መንገድ በሁሉም ክልሎች በሚስጥር የሚከናወን ህገ ወጥ ተግባር ነው።

ህገ ወጥ የሐዋላና የገንዘብ ዝውውር ላይ የሚታየውን ችግር በዝርዝር ለህግ አስፈጻሚው አካል እንደቀረበ ያስረዱት ዋና ዳይሬክተሩ ወንጀለኞቹ በፍርድ ቤት ቀርበው የተፈረደባቸው ቢሆንም በወቅቱ ባሉ ባለስልጣናት ተፅዕኖ ግለሰቦቹ እንዲፈቱ መደረጉን ገልጸዋል። 

የክልል መንግስታትም በችግሩ ላይ አስፈላጊውን እርምጃ እየወሰዱ አለመሆኑን ተናግረዋል።

አሁኑ ወቅት ባለው ለውጥ ችግሩን ለማስወገድ የሚደረገው ጥረት መልካም ቢሆንም በጉዳዩ ላይ እልባት ለመስጠት ያለው ፖለቲካዊ ቁርጠኝነት በቂ እንዳልሆነ አስረድተዋል።

በወንጀል ድርጊት የተገኘን ገንዘብ ማዘዋወር በአገር ምጣኔ ሀብት ላይ የሚያደርሰውን ጉዳትም ከመገንዘብ አንጻር የፍትህ አካላት በቂ ግንዛቤ እንደሌላቸውም አቶ ኪዳነማርያም ጠቁመዋል።

በአጠቃላይ ማዕከሉ በመንግስት በኩል የተሰጠው ትኩረትና ድጋፍ ዝቅተኛ መሆን፣ በዘርፉ የሰለጠነ የሰው ኃይል ችግር፣ ስራውን የሚመጥን የህንጻ፣ የቴክኖሎጂና የትራንስፖርት ችግር በስራው ላይ ጫና እንደፈጠረበት አብራርተዋል።

በሌላ በኩል ኢትዮጵያ ከዓለም አቀፉ የትብብር ገምጋሚ ቡድን እንዲሁም የምስራቅና የደቡብ አፍሪካ አገራት በፀረ ወንጀል የተገኘን ገንዘብ ህጋዊ አስመስሎ ማቅረብን ለመከላከል ላይ ከሚሰራው ቡድን ጋር በትብብር እንደምትሰራም ገልጸዋል።

ቡድኑ በኢትዮጵያ ያለውን ህገ ወጥ የሐዋላና የገንዘብ ዝውውር ድርጊት ለመከላከል የሚያግዝ 19 ምክረ ሀሳቦችን ያቀረበ ሲሆን 16ቱ ተግባራዊ መደረጋቸውን ተናግረዋል።

ከ16ቱ ምክረ ሀሳቦች ውስጥ መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት ስልጠና መስጠት፣ የአሰራር መመሪያ ማዘጋጀት፣ ቁጥጥርን ማጠናከርና በፋይናንስ ተቋማት ላይ እርምጃ መውሰድ የሚገኙበት ሲሆን ኢትዮጵያ እነዚህን ጉዳዮች ማሟላቷን ገልጸዋል።

ለጅምላ ጨራሽ ኬሚካሎችና ግብአቶች የፋይናንስ ድጋፍ የሚያደርጉ አካላትን ለመቆጣጠር አዋጅ ማውጣት ብቻ እንደቀረ የገለጹት ዋና ዳይሬክተሩ በአሁኑ ወቅት ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጅቶ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት መቅረቡን ተናግረዋል።

በዚህ ረገድ ምክር ቤቱ አስፈላጊውን ድጋፍና ትብብር እንዲያደርግ አቶ ኪዳነማርያም ጠይቀዋል።

በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ተስፋዬ ዳባ እንዳሉት፤ ምክር ቤቱ በአዋጅ ላቋቋመው ማዕከል ያደረገው ድጋፍና ክትትል ዝቅተኛ በመሆኑ እንደ ክፍተት የሚወሰድ ነው።

''ማዕከሉ ከአገር ደህንነት ጋር በተያያዘ ከፍተኛ ስራ የሚሰራ በመሆኑ ምክር ቤቱና ባለድርሻ አካላት በቂ ክትትልና ድጋፍ ሊያደርጉ ይገባል'' ብለዋል።

ማዕከሉ ከዚህ በፊት ለጠቅላይ ሚኒስትሩ በአዲሱ አደረጃጀት ደግሞ ለሰላም ሚኒስቴር ተጠሪ ሲሆን ምክር ቤቱ ከሰላም ሚኒስቴር ጋር በመተባበር የምክክር መድረክ እንደሚያዘጋጅም ጠቁመዋል። 

ህገ ወጥ የሐዋላና የገንዘብ ዝውውር ችግር በአገሪቱ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ላይ ተፅዕኖ ሊያሳድር የሚችል በመሆኑ የሚመለከታቸው አካላት ለጉዳዩ ልዩ ትኩረት መስጠት እንዳለባቸውም አቶ ተስፋዬ አሳስበዋል።

ማዕከሉ ለፖለቲካ አመራሮች በጉዳዩ ዙሪያ የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ ማዘጋጀት እንዳለበትና የሚሰራውንም ስራ ለህብረተሰቡ ተደራሽ ማድረግ እንደሚገባው አመልክተዋል።

የፋይናንስ ደህንነት መረጃ ማዕከል በ2002 ዓ.ም በአዋጅ የተቋቋመ ሲሆን በወንጀል ድርጊት የተገኘ ገንዘብ ወይም ንብረት ሕጋዊ አስመስሎ ማቅረብ፣ ሽብርተኝነትን በገንዘብ የመደገፍ እና ተያያዥነት ያላቸው የኢኮኖሚ ወንጀሎችን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር እንዲቻል ዓለም አቀፋዊ እና አገራዊ ግዴታዎችና ህጐች የሚከበርበት ማዕቀፍ መቅረጽና ተግባራዊ ማድረግ ይጠበቅበታል።

እንዲሁም ጥራት ያለው እና ወቅታዊ የፋይናንስ መረጃ በማቅረብ የፋይናንስና የንግድ ስርዓቱ ከእነዚህ ወንጀሎች መጠበቅ እና የአገር ደህንነት ለማስከበር አስተዋጽኦ የማድረግ ተግባርን ያከናውናል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም