ቀጥታ፡

በአምቦ ከተማ በባለሀብቶች ተይዞ ያለማ መሬት ለሥራ አጥ ወጣቶች ተሰጠ

አምቦ ጥር 18/2011 በአምቦ ከተማ በባለሃብቶች ተይዞ ለዓመታት ሳይለማ የተቀመጠ መሬት ተነጥቆ ለሥራ አጥ ወጣቶች መተላለፉን የከተማው አስተዳደር አስታወቀ።

በእዚህም ባለፉት ስድስት ወራት 46 ሄክታር መሬት ከባለ ሀብቶች ተነጥቆ ለወጣቶች መተላለፉ ተመልክቷል።

የከተማው ኢንቨስትመንት ጽህፈት ቤት ተወካይ ኃላፊ አቶ አብዲሳ መርጋ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደገለጹት በከተማው በኢንቨስትመንት ስም ተወስደው የለሙና ያለሙ መሬቶችን ለመለየት ጥናት ተካሄዷል ።

በጥናቱ መሰረት ለባለሀብቶች ተሰጥቶ ለ14 ዓመታት ያለስራ የተቀመጠ 160 ሄክታር መሬት መገኘቱን ተናግረዋል ።

"ሳይለማ ተከልሎ ከተቀመጠው መሬት ውስጥ 46 ሄክታሩ ተመላሽ ተደርጎ ለሥራ አጥ ወጣቶች ተሰጥቷል " ያሉት ኃላፊው ቀሪውን መሬት የማስመለስ ሥራ መቀጠሉን ተናግረዋል ።

"የተመለሰው መሬት በማህበር ተደራጅተው በደን ልማት፣ በእርሻና በንብ ማነብ ሥራ ለተሰማሩ ወጣቶች ተላልፏል" ብለዋል ።

እንደኃላፊው ገለጻ መሬቱ የተሰጣቸው ከ100 በላይ ወጣቶች ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎችና ኮሌጆች ተመርቀው ያለ ሥራ ለዓመታት የቆዩ ናቸው፡፡  

መሬቱ ለዓመታት ያለሥራ መቀመጡ የህዝቡ የመልካም አስተዳደር ጥያቄ ሆኖ መቆየቱን ያስታወሱት አቶ አብዲሳ " ለጥያቄው ምላሽ ለመሰጠት የተጀመረው ሥራ በቀጣይም ተጠናክሮ ይቀጥላል " ብለዋል ።

በከተማ ግብርና ዘርፍ በንብ ማነብ ሥራ ከተሰማሩ ወጣቶች መካከል ወጣት በላይ አዱኛ ከኮሌጅ ከተመረቀ ከሁለት ዓመት በኋላ ከጓደኞቹ ጋር ተደራጅቶ ወደ ስራ መግባቱን ገልጿል ።

"በንብ ማነብ ሥራ ከተሰማራን አጭር ጊዜ ቢሆንም ውጤታማ ለመሆን ተግተን እየሰራን ነው " ያለው ወጣቱ አስተዳደሩ በሰጣቸው መሬት ታግዘው ስራቸውን መጀመታቸውን ተናግሯል ።

"ከአስተዳደሩ በተሰጠን መሬት ላይ ችግኝ በማፍላት የደን ልማት ሥራ ጀምረናል" ያለው ደግሞ  ወጣት አቲናፍ ከበደ ነው።

አስተዳደሩ መሬት ተረክበው ሳያለሙ ከልለው ካስቀመጡ ባለሀብቶች በመንጠቅ ለወጣቱ የሥራ ዕድል መፍጠሪያነት ለማዋል እየወሰደ ያለው እርምጃ ተገቢ በመሆኑ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም