13 የደረቅ ወደብ ዘመናዊ የጭነት ማንሻና ማጓጓዣ መሳሪያዎች ስራ ጀመሩ - ኢዜአ አማርኛ
13 የደረቅ ወደብ ዘመናዊ የጭነት ማንሻና ማጓጓዣ መሳሪያዎች ስራ ጀመሩ
አዳማ ጥር 18/2011 የኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖትና ሎጂስቲክ አገልግሎት ድርጅት የመልቲ ሞዳል አገልግሎት ቀልጣፋና ዘመናዊ ለማድረግ በ7 ሚሊዮን ዩሮ የገዛቸው የተለያዩ የጭነት ማስተናገጃ መሳሪዎችን ሥራ አስጀመረ።
ድርጅቱ ከስዊድን ገዝቶ ያስገባቸውን ዘመናዊ የኮንተይነር ማንሻና ማጓጓዣ ማሽነሪዎች ዛሬ በሞጆ ደረቅ ወደብ በይፋ አገልግሎት መስጠት አስጀምሯል ።
የኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖትና ሎጀስትክ አገልግሎት ድርጅት ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ሮባ መገርሳ እንደገለጹት የሀገሪቱ የምጣኔ ሀብት እድገት የሚመጥን የመልቲ ሞዳል አገልግሎት መዘርጋት እየጨመረ የመጣውን የደንበኞች ፍላጎት የሚያሟላ ከመሆኑም ባለፈ በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ የሚስተዋለውን ችግር ይፈታል።
" የሞጆ ደረቅ ወደብ የሀገሪቱን ገቢ ንግድ ከ70 በመቶ በላይ የሚያስተናግድ በመሆኑ ደረጀውን የጠበቀ ቀልጠፋ አገልግሎት ለመስጠት፣ የደንበኞችን እንግልት በመቀነስ ወጪና የሚባክነውን ጊዜ ጭምር ለመቆጠብ ነው " ያስችላል ብለዋል።
"በአሁኑ ወቅት በደረቅ ወደቡ በቀን ከ1ሺህ ኮንቴነሮች በላይ ወጥተው ይገባሉ" ያሉት ዋና ሥራ አስፈጻሚው ይህን መሸከም የሚችል የሎጀስቲክ አቅርቦትና መሰረተ ልማት መዘርጋት ጊዜው የሚጠይቀው ወሳኝ ተግባር መሆኑን አስረድተዋል ።
የማሽነሪዎቹ አገልግሎት መስጠት መጀመር እስከ አስር ቀናት የሚወስደውን የኮንቴነሮችን የማራገፍና የማስፈተሽ ተግባር ወደ አንድ ቀን ዝቅ እንደሚያደርገው አስታውቀዋል።
ለኮምቦልቻና መቀሌ ደረቅ ወደቦች የተሰጡ ሁለት ማሽነሪዎችን ጨምሮ በ7 ሚሊዮን ዩሮ 10 ዘመናዊ መሳሪያዎችን በመግዛት አገልግሎት እንዲጀምሩ ተደርጓል።
በወደቡ ረዥም አገልግሎት በመስጠት ላይ የነበሩትን 6 የኮንቴነሮች ማንሻ ማሽነሪዎች ጨምሮ 16 በሚሆኑት ማሽነሪዎች የተቀላጠፈ የመልቲ ሞዳል አገልግሎት እየሰጠ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የሞጆ ደረቅ ወደብ የቴክኒክ ክፍል ባለሙያ አቶ ሰለሞን ዼጥሮስ ናቸው።
የድርጅቱ ደንበኞች ይህን አጋጣሚ በመጠቀም ከውጪ የሚገባውን እቃዎቻቸውን በፍጥነት በማንሳት የሚደርስባቸውን እንግልት፣ወጪና ጊዜያቸውን ከብክነትና አላስፈላጊ ዕዳ ማዳን እንደሚገባቸው አመልክተዋል።
ከተገልጋይ ደንበኞች መካከል የኢትዮጵያ ጉሙሩክ አስተላላፊዎች ማህበር ፕሬዘዳንት አቶ ሀብቴ ዼጥሮስ "ማሽነሪዎች ውስን በነበሩበት ወቅት ደንበኞቻችን ለእንግልትና አላስፈላጊ ለሆነ የመጋዘን ወጪ ሲጋለጡ ነበር "ብለዋል።
በአሁኑ ወቅት የመልቲ ሞዳል አገልግሎቱን ዘመናዊና ቀልጠፋ ለማድረግ መንግስት የወሰደው እርምጃ የንግዱን ማህበረሰብ ፍላጎትና ጥያቄ ያማከለ መሆኑን ተናግረዋል።