ቀጥታ፡

37 የደቡብ ከተሞች በሀገር አቀፉ የከተሞች ፎረም ይሳተፋሉ

ሀዋሳ ጥር 18/2011 በጅግጅጋ ከተማ በሚካሄደው ሀገር አቀፉ የከተሞች ፎረም 37 የደቡብ ክልል ከተሞች እንደሚሳተፉ የክልሉ ከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮ አስታውቀ።

መድረኩ በከተሞች መካከል ተቀራራቢ ልማትና እድገት በማምጣት ከተሞችን የልማት፣ የዴሞክራሲና የመልካም አስተዳደር ማዕከል የማድረግ ግብ እንዳለው ቢሮው አመልክቷል፡፡

በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የቢሮው ኃላፊ አቶ ክፍሌ ገብረማርያም በሰጡት መግለጫ እንዳሉት ለሰባተኛ ጊዜ በተካሄደ የከተሞች ፎረም የክልሉ ከተሞች ተሳትፎ ውጤታማ ነበር፡፡

በተደጋጋሚ ተሸላሚ የነበረችው ሃዋሳ ከተማን ጨምሮ የክልሉ ከተሞች ለአረንጓዴ ልማት፣ ለቱሪዝምና ኢንቨስትመንት ምቹ መሆናቸው እንዳስመረጣቸው ተናግረዋል፡፡

ዘንድሮ ለስምንተኛ ጊዜ በሶሞሌ ክልል ጅግጅጋ ከተማ በሚካሄደው ሀገር አቀፍ የከተሞች ፎረም 37 የክልሉ ከተሞች እንደሚሳተፉ ገልጸው፣ ከእነዚህ ውስጥ 27ቱ ዝግጅታቸውን ማጠናቀቃቸውን ነው የገለጹት፡፡

ቀሪዎቹ በአጭር ጊዜ ውስጥ ዝግጅታቸውን እንደሚያጠናቅቁ የጠቆሙት አቶ ክፍሌ የሚሳተፉ ከተሞች ቁጥርም ሊጨምር እንደሚችል አመልክተዋል።

መድረኩ የእርስ በርስ ግንኙነት የሚጎለብትበት፣ ጤናማ ውድድር እንዲኖር እውቅና የሚሰጥበትና መልካም ተሞክሮዎች የሚቀርቡበት መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

በመሆኑም የክልሉ ከተሞች ከዚህ ቀደም የነበራቸውን ተሞክሮ በመቀመር ባለፉት ሁለት ዓመታት ያከናወኗቸውን ተግባራት ለማቅረብና ልምድ ለመውሰድ የሚያስችል ዝግጅት ማድረጋቸውን አስረድተዋል፡፡

አቶ ክፍሌ እንዳሉት በ2009 በተጠናው የዳሰሳ ጥናት በክልሉ የከተሞች እድገትን ተከትሎ በከተማ የሚኖረው ህዝብ ቁጥር ወደ 19 ነጥብ 9 ከመቶ ደርሷል፡፡

ከየካቲት 9 እስከ 14 በጅግጅጋ ከተማ የሚከበረው 8ኛው የኢትዮጵያ ከተሞች ፎረም "መደመር ለኢትዮጵያ ከተሞች ብልጽግና" የሚል መሪ ሃሳብ እንዳለው ታውቃል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም