ቀጥታ፡

በኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለው ለውጥ የአገሪቱን ገጽታ የቀየረ መሆኑን አምባሳደሮች ገለጹ

አዲስአበባ ጥር18/2011 ከአስር ወራት ወዲህ በኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለው ለውጥ የአገሪቱን ገጽታ የቀየረና ከፍታዋን የጨመረ መሆኑን አምባሳደሮች ገለጹ።

ለውጡ በተለያዩ አገሮች ተሰማርተው የሚገኙ የኢትዮጵያ አምባሳደሮችና የዲፕሎማቲክ ማህበረሰብ አባላት ከአለም ዓቀፉ ማህበረሰብ ዘንድ ድጋፍ እንዲያገኙ ያስቻለ ሁኔታ እንደፈጠረ አምባሳደሮቹ ለኢዜአ ገልጸዋል።

በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) የኢትዮጵያ ቋሚ መልዕክተኛ አምባሳደር ታዬ አጽቀስላሴ አገሪቱ ከመላው ዓለም ጋር ያላትን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ለማሻሻል የሚያስችሉ የለውጥ ተግባራትን እያከናወነች እንደምትገኝ ጠቁመዋል።

ባለፉት ዘጠኝ ወራት ጊዜ ውስጥ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ምህዳር ከዓለም ዓቀፉ ማህበረሰብ ዘንድ ከፍተኛ የሆነ ድጋፍ ሊያገኝ ችሏል'' በማለት ለውጡ ያመጣውን ውጤት ተናግረዋል።

አምባሳደር ታዬ ጨምረው እንደገለጹት ከቀጣናው አገሮች፣ ከአህጉሩና ከመላው አለም ጋር በተለያዩ ዘርፎች በትብብር ለመስራት የሚያስችል የውጭ ፖሊሲ እንዲኖር በትኩረት እየተሰራ ነው።

''የዲፕሎማቲክ ስራችንን ከመከላከል ወደ ትብብራዊ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ማሸጋገር የሚያስችለን ምቹ ሁኔታ በመፈጠሩ የኢትዮጵያን ስም ከፍ ማድረግ ያስችለናል'' ብለዋል።

የአገሪቱ አምባሳደሮችና ዲፕሎማቶች ይህንን አሁን የተፈጠረውን ዕድል በመጠቀም የአገሪቱን ፍላጎት ለመሙላት መትጋት እንደሚጠበቅባቸውም አስገንዝበዋል።

በቅርቡ ከተሾሙት የአገሪቱ አምባሳደሮች መካከል አንዷ የሆኑት በጀርመን የኢትዮጵያ አምባሳደር ሙሉ ሰለሞን በበኩላቸው ቀደም ባለው ጊዜ በኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ይፈጸም የነበረ በመሆኑ በዲፕሎማሲ ስራዎች ላይ ጫና ያሳድር እንደነበር አስታውሰዋል።

የሰብዓዊ መብት ጥሰት ድርጊቱ አምባሳደሮች ከኢትዮጵያውያን ዳያስፖራ ጋር ለመወያየት የማያስችል እንደነበር አስታውሰዋል።

የዲፕሎማሲ ስራው የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን በመሳብ ላይ ያተኮረ የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ ላይ የሚያተኩር እንደሚሆንም ጠቁመዋል።

በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር የሆኑት አቶ ፍጹም አረጋ ከአሜሪካ ጋር ያለውን የሁለትዮሽ ግንኙነት ማጠናከር ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ እንደሚኖረው ጠቁመው የሚጠበቅባቸውን የቤት ስራ ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል።

አምባሳደር አቶ ፍጹም አረጋ አገራዊ ለውጡ በምስራቅ አፈሪካም ሆነ በመላው አፍሪካ ያለውን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የሚያጠናክር መሆኑን ተናግረዋል።

እየተሻሻለ የሚገኘው የአገሪቱ የውጭ ፖሊሲ በዓለም ዓቀፍ ፖለቲካና በዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ዙሪያ የመጣውን ለውጥ ከግምት ውስጥ በማስገባት እንደሆነ ጠቁመዋል።

የውጭ ፖሊሲው ለኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ ትኩረት የሚሰጥ በመሆኑ አብዛኛው አምባሳደር ለዚህ ጉዳይ ትኩረት በመስጠት ኢንቨስትመንትን ለመሳብ አቅሙን አሟጦ እንደሚሰራ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም