ሁሉም ኢትዮጵያዊ ህዳሴ ግድቡ እስኪጠናቀቅ የተቻለውን ድጋፍ ማድረግ ይጠበቅበታል - ታዋቂ አትሌቶች - ኢዜአ አማርኛ
ሁሉም ኢትዮጵያዊ ህዳሴ ግድቡ እስኪጠናቀቅ የተቻለውን ድጋፍ ማድረግ ይጠበቅበታል - ታዋቂ አትሌቶች
አዲስ አበባ ግንቦት 19/2010 'ሁሉም ኢትዮጵያዊ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ እስኪጠናቀቅ የተቻለውን ድጋፍ ማድረግ አለበት ሲሉ' ታዋቂ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ገለጹ። "ስለ ዓባይ እሮጣለሁ" በሚል መሪ ሀሳብ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የሰባት ኪሎ ሜትር ጎዳና ላይ ሩጫ ዛሬ በአዲስ አበባ ተካሂዷል፡፡ የኢዜአ ሪፖርተር ሩጫው በተካሄደበት መስቀል አደባባይ ውድድሩን ለመታደም የመጡ ታዋቂ አትሌቶችን አነጋግሯል። የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ምክትል ፕሬዝዳንት አትሌት ገብረእግዚአብሔር ገብረማርያም "የኢትዮጵያ ህዝብ የህዳሴው ግድብ ፍሬ እስኪታይ ከሚያደርገው ድጋፍ ወደ ኋላ ማለት የለበትም" ይላል። የህዳሴ ግድቡ ግንባታ ለማጠናቀቅ 24 ሰአት እየሰሩ የሚገኙ ወገኖቻችን ሁልጊዜም አይዞን ከጎናችሁ ነን ልንላቸው ይገባል ብሏል። ህዝቡ የግድቡ ግንባታ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ እያደረገ ያለውን ድጋፍ አሁን ካለው በላቀ መልኩ ማድረግ እንደሚገባው ነው የአትሌቲክስ ፌዴሬሽን ምክትል ፕሬዝዳንት አትሌት ገብረእግዚአብሔር ያሳሰበው። የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዝዳንትና የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል አትሌት ደራርቱ ቱሉ ህብረተሰቡ ባለው አቅም በተለያዩ መንገዶች ለህዳሴው ግድብ አስተዋጽኦ እያደረገ መሆኑን ትናገራለች። የስፖርቱ መስክ የህዳሴው ግድብ ከተጀመረ ጊዜ ጀምሮ ድጋፍ እያደረገ መሆኑንና አሁንም ድጋፉን ይቀጥላል ብላለች። የዛሬውም ሩጫ የኢትዮጵያ ህዝብ ለግድቡ ያለውን አንድነትና መግባባት በጋራ በመሮጥ ያሳየበት እንደሆነና በቀጣይም ህብረተሰቡ ለግድቡ ያለውን ድጋፍ እንደሚቀጠል ያላትን እምነት ተናግራለች። የወጣቶችና ስፖርት ሚኒስትር አቶ ርስቱ ይርዳ በበኩላቸው ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ አትሌቶች ድጋፍ ማድረጋቸውን እንደቀጠሉ መሆኑን ተናግረዋል። የአትሌቶቹ ድጋፍ ከቦንድ ግዢና ከገንዘብ ድጋፍ በተለያየ መንገድ አስተዋጽኦ እያበረከቱ እንደሆነም አስረድተዋል። የህዝብ ተሳትፎ ያልተለየው የህዳሴ ግድብ አሁንም እስኪጠናቀቅ ሁሉም አስፈላጊውን ድጋፍ ማድረግ እንዳለበት አመልክተዋል።