በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ድሬዳዋ ከተማና ሲዳማ ቡና ሊያደርጉት የነበረው ጨዋታ ላልተወሰነ ጊዜ ተራዘመ - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ድሬዳዋ ከተማና ሲዳማ ቡና ሊያደርጉት የነበረው ጨዋታ ላልተወሰነ ጊዜ ተራዘመ
አዲስ አበባ ጥር 17/2011 በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 13ኛ ሳምንት ድሬዳዋ ከተማና ሲዳማ ቡና ሊያደርጉት የነበረው ጨዋታ ላልተወሰነ ጊዜ መራዘሙን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽኑ አስታወቀ።
ሁለቱ ቡድኖች በወጣላቸው መርሃ ግብር መሰረት ከነገ በስቲያ በድሬዳዋ ስታዲየም ላይ ጨዋታቸውን ማድረግ ነበረባቸው።
ነገር ግን በድሬዳዋ ከተማ ባለው ወቅታዊ ሁኔታ የተነሳ ከሁለቱ ክለቦች ጋር በተደረገ ውይይት ጨዋታው ላልተወሰነ ጊዜ መራዘሙን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የውድድር ከፍተኛ ባለሙያ አቶ ከበደ ወርቁ ለኢዜአ ገልጸዋል።
ጨዋታው በተስተካካይ መርሃ ግብር ተይዞ በቀጣይ የሚካሄድበት ጊዜ ከጥቂት ቀናት በኋላ እንደሚገለጽና ሌሎቹ የ13ኛ ሳምንት የሊጉ ጨዋታዎች በተያዘላቸው መርሃ ግብር እንደሚካሄዱ አመልክተዋል።
በዚሁ መሰረት ጨዋታዎቹ እሁድ ጥር 19 ቀን 2011 ዓ.ም እና ሰኞ ጥር 20 ቀን 2011 ዓ.ም በአዲስ አበባና በክልል ከተሞች ይካሄዳሉ።
ከነገ በስቲያ በአዲስ አበባ ስታዲየም ከቀኑ 10 ሰአት የፕሪሚየር ሊጉ መሪ ኢትዮጵያ ቡና የአምናው የሊጉ አሸናፊ ጅማ አባ ጅፋርን ያስተናግዳል።
በክልል ከተሞች እሁድ አራት ጨዋታዎች ይደረጋሉ።
በሃዋሳ ስታዲየም ደቡብ ፖሊስ ከመቐለ ሰብዓ እንደርታ፣ ወላይታ ድቻ በሜዳው ከባህርዳር ከተማ፣ ፋሲል ከተማ በሜዳው ከአዳማ ከተማና በመቐለ ዓለም አቀፍ ስታዲየም ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ ከቅዱስ ጊዮርጊስ በተመሳሳይ ከቀኑ ዘጠኝ ሰአት ላይ ጨዋታቸውን ያድርጋሉ።
ሰኞ ጥር 20 ቀን 2011 ዓ.ም በአዲስ አበባ ስታዲየም ከቀኑ 11 ሰአት መከላከያ ከሃዋሳ ከተማ ጨዋታውን የሚያደርግ ሲሆን በመቐለ ዓለም አቀፍ ስታዲየም ደደቢት ከስሑል ሽረ ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት ላይ ይጫወታሉ።
የፕሪሚየር ሊጉን የደረጃ ሰንጠረዥ ኢትዮጵያ ቡና በ22 ነጥብ ሲመራ፣ ቅዱስ ጊዮርጊስ በ21 ነጥብ ሁለተኛ ሃዋሳ ከተማና ሲዳማ ቡና በተመሳሳይ 20 ነጥብ በግብ ክፍያ ተበላልጠው በቅደም ተከተል ሶስተኛና አራተኛ ደረጃን ይዘዋል።
ስሑል ሽረ፣ ደቡብ ፖሊስና ደደቢት ከ14ኛ እስከ 16ኛ ያለውን ደረጃ በመያዝ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛሉ።