ቀጥታ፡

የሴቶች ኢንተርፕነርሺፕ ልማት ፕሮጀክት ከጃፓንና ከጣሊያን በተገኘ 65 ሚሊዮን ዶላር ለሁለት አመት ተራዘመ

አዲስ አበባ ጥር 17/2011 የሴቶች ኢንተርፕነርሺፕ ልማት ፕሮጀክት ከጃፓንና ከጣሊያን በተገኘ 65 ሚሊዮን ዶላር ለተጨማሪ ሁለት አመት እንዲራዘም መደረጉን የፌዴራል ከተሞች ስራ ዕድል ፈጠራና ምግብ ዋስትና ኤጀንሲ አስታወቀ።

ባለፉት አምስት አመታት ለሴቶችን የስራ ዕድል የመፍጠር ሂደቱን ሲደግፍ የነበረው 'የሴቶች ኢንተርፕነርሺፕ ልማት ፕሮጀክት' ውጤት እንዳስገኘም ተናግሯል።

የጃፓን መንግስትና የጣሊያን መንግስት ካደረጉት ድጋፍ በተጨማሪ ከአውሮፓ ኢንቨስትመንት ባንክ የ30 ሚሊዮን ዩሮ ብድር ስምምነት ላይ ተደርሶ የኢትዮጵያ መንግስት መፈራረሙን ኤጀንሲው አመልክቷል።

የፕሮጀክቱን አፈጻጸም አስመልክቶ በተሰጠው መግለጫ እንደተገለጸው፤ በፕሮጀክቱ አማካኝነት ከ10ሺህ በላይ ለሚሆኑ ስራ ፈጣሪ ሴቶች የ2 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር ብድር እንዲሰጥ ተደርጓል።

የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር አቶ ዘነበ ኩሞ ፕሮጀክቱ ለ16 ሺህ ሴቶች ስልጠና አገልግሎት መሰጠቱንም አመልክተዋል።

ከብድር በተጨማሪ ስራ ፈጣሪ ሴቶችን በተለያዩ የስራ ፈጠራ ላይ በቴክኒክና ሙያ አማካይነት ስልጠና የተሰጠ ሲሆን አሁንም የንግድ ፈቃድ አውጥተው በስራ ዕድል ፈጠራ ላይ የተሰማሩ ሴቶች በነጻ ስልጠና እንዲያገኙ የሚያስችል ሁኔታ መመቻቸቱን ተናግረዋል።

ዓለም ባንክ ባካሄደው ጥናት መሰረት 55 ነጥብ 7 በመቶ ስራ የመቅጠር አቅማቸው አድጓል፣ ትርፋማነታቸውም 44 ነጥብ 8 በመቶ እድገት ማሳየቱ መረጋገጡን ጠቁመዋል።

ፕሮጀክቱ ውጤታማ በመሆኑ የጃፓን መንግስት 50 ሚሊዮን ዶላር እና የጣሊያን መንግስት 15 ሚሊዮን ዩሮ ብድር ለፕሮጀክቱ የመደቡ በመሆኑ ለ2 ዓመት እንዲራዘም መደረጉን አቶ ዘነበ ተናግረዋል።

ከዚህ በፊት ተጠቃሚ አዲስ አበባ፣ አዳማ፣ ባህርዳር፣ ድሬደዋ፣ ሃዋሳ እና መቀሌ ከተሞች በተጨማሪ አክሱም፣ ጎንደር፣ አሰላና ዲላ በተጨማሪ ተጠቃሚ እንዲሆ መደረጉን ተናግረዋል።

ብድሩን የወሰዱ ሴቶች 83 በመቶ በንግድና በአገልግሎት ዘርፍ የተሰማሩ ሲሆን በቀጣይ በማምረቻ ዘርፍ እንዲሰማሩ የማበረታት ተግባራት የሚከወን መሆኑን ገልጸዋል።

የሰልጠና፣ የብድር፣ የዱቤ ማምረቻ መሳሪያዎችን በማመቻቸት በርካታ ሴቶች ተጠቃሚ የሆኑ ሲሆን በቀጣይ ተጨማሪ ሴቶች ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ገልጸዋል።

በእነዚህ ከተሞች 12 የአነስተኛ ብድርና ቁጠባ ተቋማት ጋር ብድሩን በማቅረብ በኢትዮጵያ ልማት ባንክ በኩል የፕሮጀክቱ የብድር ፋይናንስ እየቀረበ መሆኑን አስረድተዋል።

የፕሮጀክቱ ተጠቃሚ ሴቶች 98 በመቶ የወሰዱትን ብድር በጊዜ በመመለስ ለሌሎች አረአያ መሆናቸውንም ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም