የመቀሌና የአክሱም ደም ባንክ ማዕከላት ያቀዱትን የደም መጠን ለመሰብሰብ መቸገራቸውን ገለጹ - ኢዜአ አማርኛ
የመቀሌና የአክሱም ደም ባንክ ማዕከላት ያቀዱትን የደም መጠን ለመሰብሰብ መቸገራቸውን ገለጹ
መቀሌ ጥር 17/2011 በሰው ኃይልና በበጀት እጥረት ምክንያት ያቀዱትን የደም መጠን ለመሰብሰብ መቸገራቸውን በትግራይ የመቀሌና የአክሱም ደም ባንክ ማዕከላት ገለጹ።
የክልሉ ጤና ቢሮ በበኩሉ ችግሩ የአካባቢን ሃብትና የህብረተሰቡን ነጻ ተሳትፎ በአግባቡ መጠቀም ካለመቻል የተፈጠረ መሆኑን ጠቁሟል።
የአክሱምና የመቀሌ ደም ባንክ ማዕከላት አስተባባሪዎች እንዳሉት የበጀትና የጤና ባለሙያ እጥረት ለመሰብሰብ ያቀዱትን የደም መጠን እንዳይሰበስቡ እንቅፋት ሆኖባቸዋል።
በተጠናቀቀው ግማሽ በጀት ዓመት ሁለቱ ማዕከላት መሰብሰብ ከሚጠበቅባቸው 11 ሺህ ዩኒት ደም ውስጥ መሰብሰብ የቻሉት ግማሽ ያህሉን ብቻ መሆኑ ተመልክቷል።
የአክሱምና የመቀሌ ደም ባንክ ማዕከላት አስተባባሪዎች አቶ ሳምሶም የማነ እና ሲስተር ትንስኡ ግርማይ ለኢዜአ እንዳሉት፣ በዘንድሮ በጀት ዓመት ለውሎ አበል፣ ለትምህርት፣ ለስልጠናና ህትመት ውጤት ሥራዎች በድምሩ ከ3 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት ቢጠይቁም በክልሉ ጤና ቢሮ የተፈቀደው ከ700 ሺህ ብር ያነሰ ነው።
ለትራንስፖርት አገልግሎት ከተጠየቁት 12 አምቡላንሶች ውስጥ በሁለቱ ማዕከላት አገልግሎት እየሰጡ ያሉት አራት ብቻ መሆናቸውንም አስተባባሪዎቹ ተናግረዋል።
በተጠቀሱ ችግሮች ምክንያት ስለ በጎፍቃድ የደም ልገሳ ጠቀሜታ ትምህርትና ስልጠና በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ ለህብረተሰቡ መስጠት አለመቻሉን አስተባባሪዎች አስታውቀዋል፡፡
የመቀሌ ደም ባንክ ማዕከል አስተባባሪ ሲስተር ትንስኡ ግርማይ እንዳሉት፣ በተጠናቀቀው ግማሽ በጀት ዓመት ማዕከሉ መሰብሰብ ከነበረበት 6 ሺህ 500 የደም ከረጢት መካከል መሰብሰብ የቻለው 4 ሺህ 300 ከረጢት ነው።
የአክሱም ደም ባንክ ማዕከል አስተባባሪ አቶ ሳምሶም የማነ በበኩላቸው፣ በዚሁ ጊዜ ውስጥ ለመሰብሰብ ከታቀደው 4ሺህ 250 የደም ከረጢት ውስጥ ግማሽ የሚሆነውን መሰብሰብ እንደተቻለ ገልጸዋል።
የታቀደውን የደም መጠን መሰብሰብ ባለመቻሉም ለጤና ተቋማት የሚፈለገውን የደም መጠን በሚፈለገው ጊዜ ውስጥ ለማቅረብ መቸገራቸውን ተናግረዋል።
በትግራይ ክልል ጤና ቢሮ የእናቶችና ህጻናት እንክብካቤ ባለሙያ ሲስተር ትርሃስ አስመላሽ ባለፉት ስድስት ወራት ከደም መፍሰስ ጋር በተያያዘ 53 እናቶች ለሞት መዳረጋቸውን ገልጸዋል።
ከእነዚህ እናቶች ውስጥ 19ኙ ደም በወቅቱ ባለማግኘታቸው ህይወታቸው ያለፈ መሆኑንም አመልክተዋል።
በመቀሌ ከተማ የሃውልት ክፍለ ከተማ ነዋሪ አቶ ግደይ አብርሃ በበኩላቸው ባለቤታቸው በወሊድ ወቅት የደም መፍሰስ ችግር እንዳጋጠማቸው ተናግረዋል።
ለባለቤታቸው ደም ለማግኘት በመቀሌ ሆስፒታል ጥረት ቢያደርጉም እስካሁን ድረስ እንዳልተሳካላቸው ገልጸዋል።
የትግራይ ክልል ጤና ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ሐጎስ ጎደፋይ ጉዳዩን አስመልክተው በሰጡት ምላሽ በገንዘብ እጥረት የማዕከላቱን የበጀትና የአምቡላንስ ጥያቄ መመለስ አለመቻሉን ጠቁመዋል።
የታቀደውን የደም መጠን በአግባቡ መሰብሰብ ባለመቻሉም በክልሉ ሪፈራል ሆስፒታሎች ሳይቀር የጠየቁትን ደም በተፈለገው ጊዜ ውስጥ እያገኙ እንዳልሆነ አስረድተዋል።
ከወረዳ እስከ ደም ባንክ ማዕከላት ድረስ የሚገኙ የጤና አመራሮችና ባለሙያዎች የተገኘውን ሃብትና የህብረተሰብ ተሳትፎ ተጠቅመው ለመስራት ቁርጠኛ አለመሆናቸው ለችግሩ ምንጭ መሆኑንም ዶክተር ሐጎስ ገልጸዋል።
ያለው የደም እጥረት የሚፈታው አመራሩ ህዝባዊ መድረኮችና መገናኛ ብዙሀንን ተጠቅሞ ደም መለገስ ያለውን ጠቀሜታ በህዝቡ ውስጥ ግንዛቤ መፍጠር ሲችል መሆኑንም አመለክተዋል።