ቀጥታ፡

ያልተሰራባቸው አገራዊ እሴቶች ችግሮችን የመፍታት አቅም አላቸው

አዲስ አበባ ጥር 17/2011ያልተሰራባቸው አገራዊ እሴቶች የውስጥ ችግሮችን የመፍታት አቅም እንዳላቸው በገዳ ስርዓት የወረደው እርቅ ማሳያ እንደሆነ አስተያየት ሰጪዎች ገለፁ።

ኢትዮጵያ የተለያዩ ማህበረሰባዊ ችግሮችና ግጭቶች የሚፈቱባቸው ባህላዊ እሴቶች ቢኗሯትም በአግባቡ ጥቅም ላይ አለመዋላቸውን ልብ ይሏል።

የገዳ አባቶች ትናንት አምቦ ላይ የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲና የኦሮሞ ነጻ አውጪ ግንባርን ለማስታረቅ ያደረጉት እንቅስቃሴ አገራዊ እሴቶቻችን የችግሮቻችን መፍቻ ቁልፍ መሆናቸውን እንዳሳዩ አስተያየት ሰጪዎቹ ተናግረዋል።

በእርቁ ላይ የተገኙት አባቢያ አባጃብር አባ ገዳ ትልቅ ስራ ነው የሰሩት  ረስተነው የነበረውን አዲስ ትምህርት ነው ያስተማሩን ፣ ተአምር ነው የሰሩት፤ የገዳ ሲስተም በህዝቡ ምኞት ላይ የተመሰረተ መሆኑን ነው ያሳዩን ብለዋል፡፡

የጀስቲስ ፎር ኦል ፕሬዚዳንት ፓስተር ዳንኤል ገብረስላሴ አገራዊ እሴቶችን ትተን በምዕራቡ ዓለም የችግር መፍቻዎች ላይ 'መንጠላጠላችን ዋጋ አስከፍሎናል' ብለዋል።

አሁን ለባህላዊ እሴቶቻችን ትኩረት ለመስጠት በአመራሩ በኩል ፍላጎት መታየት መጀመሩን ጠቅሰው በውጭ አካላት ይፈታ ቢባል ተጨማሪ ወጪ ያስከትል እንደነበር ነው የተናገሩት።

የቀደሙት ግጭት መፍቻ አገር በቀል ስርዓቶቻችን በዚህ መልክ ችግሮችን መፍታት ከቻሉ አመራሩ አካል ለባህላዊ እሴቶች ቦታ በመስጠትና ማሳደግ እንደሚገባውም ጠቁመዋል።

በዘመናዊው ትምህርት የተካተቱ የግጭት መፍቻ ዘዴዎች ከዚህ ያልተለዩ በመሆናቸው የራሳችንን ችግር በራሳችን መፍታት የሚያስችሉ እሴቶችን ማውጣት ላይ ትኩረት መሰጠት 'አለበት' ብለዋል።

አባ ገዳ ተፈራ ዱጋሳ በበኩላቸው ወደ ሌሎች ዓለማት ዓይን ከማማተር ወደ ውስጥ መመልከት፣ ወጣቱም የአባቶቹን መልካም እሴቶች በማንበብና በማጥናት ወደ ተግባር ሊቀይር እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

እነዚህና መሰል እሴቶች በማስፋፋት ለትውልዱ እንዲተላለፉ ማድረግም የአባቶች የቤት ስራ መሆኑን አመልክተዋል።

በሁሉም የኢትዮጵያ አካባቢ መሰል ባህላዊ እሴቶች በስፋት እንደሚገኙ የጠቆመው ወጣት ኦብሳ አብዲሳም ከምዕራባዊያን ተፅዕኖ በመውጣት እነዚህን መጠቀም የወጣቶች ኃላፊነት መሆኑን ተናግሯል።

በአገራችን ውስጥ በዋርካ ስር ተሰብስበው፣ ጥላ ስር ተቀምጠው እርቀ ሰላም የማይፈፀምበት ማህበረሰብ የለም ያለው ወጣት አብዲሳ  ማህበረሰቡን ካዳመጥን የቀሩብንን ነገሮች የጣልናቸውን ነገሮች መለስ ብለን ከተመለከትን ውጤታማ የማንሆንበት ነገር የለም ብላል።

አባ ገዳዎች በኦሮሞ ነጻ አውጪ ግንባርና በመንግስት መካከል የተፈጠረውን ችግር በተሳካ መልኩ የፈቱ ሲሆን፤ ከሳምንታት በፊት በትግራይና በአማራ ክልሎች አመራሮች መካከል ተፈጥሮ የነበረውን አለመግባባት ለመፍታት የሃይማኖት አባቶችና የአገር ሽማግሌዎች ተመሳሳይ ተግባር መፈፀማቸው ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም