የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከወጪ ንግድና ሃዋላ ሶስት ቢሊዮን ዶላር ገቢ አግኝቷል - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከወጪ ንግድና ሃዋላ ሶስት ቢሊዮን ዶላር ገቢ አግኝቷል
አዲስ አበባ ጥር 17/2011 የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ባለፉት ስድስት ወራት ከወጪ ንግድና ሃዋላ ሶስት ቢሊዮን ዶላር ገቢ ማግኘቱን ገለጸ።
ባንኩ የበጀት ዓመቱን አጋማሽ የስራ አፈፃፀም ዛሬ መገምገም ጀምሯል።
የባንኩ ፕሬዝዳንት አቶ ባጫ ጊና በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት አጠቃላይ የተቀማጭ ገንዘብ መጠኑን 32 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር ለማድረስ ታቅዶ ወደ 29 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር ማሳደግ ተችሏል።
ይህ አፈጻጸም ከእቅዱ ጋር ሲነጻጸር ከፍተኛ የሚባል መሆኑን ነው አቶ ባጫ የተናገሩት።
ከውጭ ምንዛሬ ግኝት ጋር በተያያዘ ከወጪ ንግድ፣ ከውጭ ሀዋላና ሌሎች ምንጮች ሶስት ቢሊዮን ዶላር የተገኘ ሲሆን ይህም የእቅዱን 93 በመቶ የሚሸፍን ነው።
''31 ቢሊዮን ብር ብድር ለመሰብሰብ ታቅዶ ነበር'' ያሉት አቶ ባጫ መሰብሰብ የተቻለው 22 ቢሊዮን ብር እንደሆነ ተናግረዋል።
ለዕቅዱ ሙሉ በሙሉ አለመሳካት ምክንያቱ ለዋና ዋና ፕሮጀክቶች የተሰጡ ብድሮች በተቀመጠላቸው የክፍያ መርሃ ግብር ባለመሰብሰባቸው እንደሆነ አብራርተዋል።
ባንኩ በስድስት ወራት ውስጥ 59 አዳዲስ ቅርጫፎችን ከፍቶ 188 ሚሊዮን ብር ተጨማሪ ተቀማጭ ገንዘብ መሰብሰቡን አስረድተዋል።
አገልግሎት የሚሰጡ የኤ.ቲ.ኤም ማሽኖች፣ የተቀማጭ ሂሳቦችና የቅርጫፎች ቁጥር መጨመሩንም ጠቁመዋል።
አቶ ባጫ እንደሚሉት የባንኩ አጠቃላይ የትርፍ መጠንም 9 ነጥብ 4 ቢሊዮን ደርሷል።
የውጭ ምንዛሬ በሚፈለገው መጠን ለደንበኞች ማቅረብ አለመቻል ካጋጠሙ ችግሮች መካከል እንደሆነ ጠቅሰው በተለያዩ አካባቢዎች የተከሰተው አለመረጋጋት ለሀብት ማሰባሰብና ገንዘብ ዝውውር ፈተና እንደነበር ጠቅሰዋል።
በኤ.ቲ.ኤም አገልግሎት የኔትወርክ ችግር እያጋጠመ መሆኑን የገለጹት አቶ ባጫ አገልግሎቱን የተሻለ ለማድረግ 'እየተሰራ ነው' ብለዋል።
የክፍያ አገልግሎቶችን በካርድ፣ በበይነ መረብና ሞባይል ብቻ ላይ የተመሰረቱ ለማድረግ 'በሰፊው እየተሰራ ነው' ሲሉም አክለዋል።
የባንኩን የማኔጅመንት አባላት የስራ አፈጻጸሙን በዝግ እየገመገሙ ሲሆን ነገ እንደሚጠናቀቅ ይጠበቃል።