በጉኑኖ ሃሙስ ከተማ ግጭት የተጠረጠሩ 30 ግለሰቦች በቁጥጥር ሥር ዋሉ - ኢዜአ አማርኛ
በጉኑኖ ሃሙስ ከተማ ግጭት የተጠረጠሩ 30 ግለሰቦች በቁጥጥር ሥር ዋሉ
ሶዶ ጥር 16/5/2011 በወላይታ ዞን በጉኑኖ ሃሙስ ከተማ አስተዳደር በዚህ ሳምንት በተከሰተው ግጭት የተጠረጠሩ ከ30 በላይ ግለሰቦች ፖሊስ በቁጥጥር ሥር አውሏቸዋል።
ነዋሪዎች ከተማዋ ወደ ቀድሞው ሰላሟ በመመለሷ የዕለት ዕለት እንቅስቃሴያቸውን ማከናወን ጀምረዋል፡፡
የአስተዳደሩ ፖሊስ አዛዥ ዋና ኢንስፔክተር ማጉጄ መጃ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በከተማዋ ግጭት እንዲቀሰቅስና ንብረት በማውደም የተጠረጠሩ ግለሰቦች በቁጥጥር ሥር ውለዋል፡፡
በቁጥጥር ሥር ከዋሉት ውስጥ ወጣቶችን ለአላስፈላጊ ድርጊት በማደራጀትና በማነሳሳት የተጠረጠሩ አንድ ነጋዴና አንድ የመንግሥት ሠራተኛ እንደሚገኙበት ተናግረዋል።
በተጠርጣሪዎቹ ላይ በቂ መረጃ በማደራጀት ጉዳያቸውን ለፍርድ ለማቅረብ እየተሰራ መሆኑንም አዛዡ አስታውቀዋል፡፡
በቁጥጥር ሥር የሚውሉት ተጠርጣሪዎች ቁጥር ሊጨምር እንደሚችልም ገልጸዋል።
ነዋሪዎች የሕግ የበላይነትን በኃይል ለመናድ የሚፈልጉ ኃይሎችን አሳልፎ በመስጠት ሰላሙን መጠበቅ ይገባቸዋል ሲሉም ተናግረዋል፡፡
ከከተማዋ ነዋሪዎች መካከል አቶ ደሳለኝ ደኣ ግጭቱን የቀሰቀሱ ኃይሎች ግጭቱ በከተማው ዙሪያ ያለው ማህበረሰብ ሳምንታዊ የገበያ ቀን ተጠብቆ መከሰቱ የተለየ አጀንዳ ያላቸው ሰዎች እንዳደራጁት አመላካች ነው ብለዋል፡፡
የከተማዋ አንዳንድ ሞተር ቢስክሌተኞችና ጀሌዎቻቸው በሕግ ከተፈቀደው በላይ ለመጫን ከፖሊስ ጋር ግብግብ መፍጠራቸው ተገቢ ያልሆነ ድርጊት ነው በማለትም አውግዘውታል ፡፡
''ወንጀለኞችን በማጋለጥ የሕግ የበላይነትን እንዲከበርና የከተማችንን ሰላም ለማረጋገጥ አጠናክረን እንሰራለን።በየቤቶቻችንና አካባቢያችን ምክክራችንን እንቀጥላለን'' ብለዋል፡፡
ሞተር ቢስክሌተኞች ከተፈቀደው በላይ መጫንን እንደ መብት በመቁጠር ኃይል አደራጅቶ ጉዳት ማድረስ የከተማውን ወጣቶች እንደማይወክል የተናገረው ወጣት ሳምሶን ሻታ ነው፡፡
መብትን ለማስከበርና ጥያቄዎችን ለማቅረብ በኃይልና አደጋን በማስከተል ምላሽ ለማግኘት መሞከር ኋላቀርነትና ዓላማ ቢስ መሆንን ያሳያል ያለው አስተያየት ሰጪ፣ ሕግን በተከተለ መልኩ መነጋገርና ባለው ላይ መጨመር ሲቻል አውድመንና ቀንሰን እንዲሁም ሕዝብን መረበሽ ከወጣቱ አይጠበቅም ብሏል፡፡
የጉኑኖ ሃሙስ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ታምራት በለጠ በከተማው በተከሰተው የጸጥታ መደፍረስ በመንግሥትና በግል ንብረት ላይ ጉዳት መድረሱን ገልጸዋል፡፡
ነዋሪዎች የግጭቱን መንስዔዎችና ጠንሳሾችን አሳልፎ ለሕግ በመስጠት ከተማዋ ወደቀድሞ ሰላሟ እንድትመለስ ማድረጋቸውን ተናግረዋል፡፡
ጉዳቱ ከደረሰባቸውተቋማት በስተቀር አገልግሎት ሰጪ ተቋማትም ሥራ መጀመራቸውንም አመልክተዋል፡፡
ለችግሩ ዘላቂ መፍትሄ ለመስጠት ውይይት በየደረጃው መካሄዱንና በቀጣይም በሃይማኖት ተቋማትና በአደረጃጀቶች እንደሚቀጥል ከንቲባው ገልጸዋል።
በግጭቱ ጉዳት የደረሰባቸውን ግለሰቦችና የመንግሥት ተቋማትን ለማቋቋም የዋጋ ትመና የሚያደርግ ኮሚቴ መመስረቱንም አስታውቀዋል፡፡
ጉኑኖ ሃሙስ የዳሞት ሶሬ ወረዳ ርዕሰ ከተማ ናት።