የጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ የሱዳን ጉብኝት ስኬታማ ነው- አህመድ ሺዴ

112
አዲስ አበባ ሚያዝያ 25/2010 ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በሱዳን ያደረጉት ጉብኝት ስኬታማ መሆኑን የመንግስት ኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ኃላፊ ሚኒስትር አስታወቁ። ኃላፊ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሺዴ ቦሌ አለም ዓቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የመሩት ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃለፊዎች ልዑክ በሱዳን ያደረገው የስራ ጉብኝት ስኬታማ ነው። ጉብኝቱ በአገሮቹ መካከል ያለውን ታሪካዊ ትስስር ወደ ላቀ ደረጃ እንደሚያደርሰውም ሚኒስትሩ ገለጸዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ በቆይታቸው ከሱዳን ፕሬዝዳንት ኦማር ሐሰን አልበሽር ጋር የዜጎችን ጉዳይና ክብርን በተመለከተ ተወያይተዋል። መልካም ዲፕሎማሲያዊ ግምንኙነት መፍጠራቸውንም ገልጸዋል። በምጣኔ ሀብት ረገድ አገሮቹ የሚያዋሱኗቸውን ኮሪደሮች ከማልማት አንስቶ በአጠቃላይ ኢኮኖሚያዊ ውህደት ላይ የጋራ መግባባት መፍጠራቸውን አመልክተዋል። በፖለቲካው መስክ በተለይ በሰላምና ደህንነት ጉዳይ ላይ ያላቸውን የትብብር መስክ አጠናክረው ለመቀጠል መስማማታቸውን የጠቆሙት ሚኒስትሩ፤ በቀጠና ጉዳይ ላይም ተወያይተዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ አህመድ በሱዳን ያደረጉትን የሁለት ቀን ይፋዊ የስራ ጉብኝ አጠናቀው ተመልሰዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም