በኢትዮጵያ የሚካሄደውን ለውጥ እንደሚደግፉ አዲስ የተሾሙ የተለያዩ አገራት አምባሳደሮች ገለጹ

68

አዲስ አበባ ጥር 16/2011 በኢትዮጵያ የተጀመረውን የፖለቲካና ምጣኔ ኃብታዊ ለውጥ እንደሚደግፉ በአገሪቱ አዲስ የተሾሙ የተለያዩ አገራት አምባሳደሮች ገለፁ።

ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ዛሬ በኢትዮጵያ አዲስ የተሾሙ የስምንት አገራት አምባሳደሮችን የሹመት ደብዳቤ በብሄራዊ ቤተ መንግስት በተከናወነ ስነ-ስርዓት ተቀብለዋል።

የሹመት ደብዳቤያቸውን ያቀረቡት የካናዳ፣ቱርክ፣ ሴራሊዮን፣ ኢኳቶሪያል ጊኒ፣ ስሎቫኪያ ሪፐብሊክ፣ ሰርቢያ እንዲሁም ተቀማጭነታቸው በካይሮ እና ናይሮቢ የሆኑት የማልታ እና የኮሎምቢያ አምባሳደሮች ናቸው።

አምባሳደሮቹ ከፕሬዚዳንቷ ጋር በነበራቸው ቆይታ በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለውን ሁለንተናዊ የለውጥ እርምጃ አድንቀዋል።

አገሪቱ በተለይ ከኤርትራ ጋር የመሰረተችውን ሰላም እና በአፍሪካ ቀንድ ሰላም እና መረጋጋት እንዲሰፍን በመጫወት ላይ ያለችውን ሚና እንደሚያደንቁም ገልጸዋል።

በቆይታቸውም ከኢትዮጵያ ጋር ያላቸውን የትብብር ግንኙነት ለማጠናከር እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል።

ፕሬዝዳንት ሰህለወርቅ ዘውዴ በኢትዮጵያ እየተካሄደ ስላለው ሁሉን ዓቀፍ ለውጥ ለአምባሳደሮቹ አብራርተዋል።

ኢትዮጵያ ከአገሮቹ ጋር ያላትን ሁለንተናዊ የሁለትዮሽና የባለብዙ ወገን ትብብሮች አጠናክራ እንደምትቀጥል ለአምባሰደሮቹ ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ ቆይታቸውም የመንግስት ድጋፍ እንደማይለያቸው ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም