ቀጥታ፡

ትላልቅ የልማት አውታሮች በአገሪቱ የዱር እንስሳት ኃብት ላይ አደጋ እየጋረጡ ነው ተባለ

አዲስ አበባ  ጥር 16/2011 በኢትዮጵያ የተለያዩ ክፍሎች እየተካሄዱ ያሉት ትላልቅ የልማት አውታሮች በአገሪቱ የዱር እንስሳት ኃብት ላይ አደጋ አየጋረጡ እንደሆነ ተገለፀ። 

ይህ የተገለፀው የኢትዮጵያን የዱር እንስሳት ሃብት፣ ልማትና ጥበቃን በተመለከተ ዛሬ በተካሄደው የባለድርሻ አካላት ውይይት ላይ ነው።

የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ ከኢትዮጵያ የዱር እንሰሳት ጥበቃ የምሁራን ስብስብ (ቲንክ ታንክ) ጋር  በመተባበር በተዘጋጀው ውይይት ላይ በቀረበው ጥናት ላይ እንደተመለከተው የአገሪቱ የዱር እንስሳት ኃብት ከፍተኛ የመመናመን አደጋ ተጋርጦበታል።

ለአደጋው በምክንያቶች ከተጠቀሱት መካከል አንዱ በአገሪቱ ያለው የመሬት አጠቃቀም ችግር ነው ተብሏል።

ጽሁፉን ያቀረቡት የኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ጥበቃ ምሁራን ስብስብ (ቲንክ ታንክ) ዋና ፀሃፊ ዶክተር መክብብ እሸቱ እንደገለጹት፣ በአገሪቱ ግልጽ የሆነ የመሬት አጠቃቀም ባለመኖሩ የዱር እንስሳት መኖሪያ በሆኑት ብዙዎቹ  ፓርኮች የልማት ፕሮጀክቶች እየተከናወነባቸው ነው።

ለአብነትም 50 ዓመታት በላይ እድሜ ባለው የጋምቤላ የዱር እንስሳት ፓርክ ውስጥ የኦሞ ኩራዝ የስኳር ፋብሪካ፣ በአዋሽ ፓርክ ደግሞ ከሰም የስኳር ፋብሪካ  እንደዚሁም የባቡር መስመርን ጨምሮ የተለያዩ የመሰረተ ልማት አውታር ግንባታዎች በተለያዩ የዱር እንስሳት ኃብት መኖሪያ ስፍራዎች ላይ እየተከናወነ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በዚህም የተነሳ በአሁኑ ወቅት የበርካታ የጥብቅ ቦታዎች የቆዳ ስፋት በእጅጉ እየቀነሰ ከመምጣቱም በላይ የዱር እንሰሳት ዝርያዎችም በመጥፋት ላይ መሆናቸውም ተመልክቷል።

ከማጎ ብሄራዊ ፓርክ ቀጭኔ፣ የሜዳ አህያ ፣ሳላ፣ የሜዳ ፊየልና የሰጎን ዝርያቸው ሙሉ በሙሉ ጠፍተዋል፤ የፓርኩ የቆዳ ስፋትም በእጅጉ ቀንሰሷል ሲሉ ነው ዶክተር መክብብ የገለፁት። 

"በአዋሽ ብሄራዊ ፓርክ ይኖሩ የነበሩት የሜዳ አህያ፣ ሰጎንና አቦ ሸማኔ በአሁኑ ወቅት ዝርያቸው ጠፍቷል፤ ሌሎች በፓርኩ የሚኖሩት እንስሶች  ቁጥርም እየተመናመነ ነው" ብለዋል።

በመሆኑም መንግስት የኢንቨስትመንት ፖሊሲውን ለመተግበር ሲንቀሳቀስ በተፈጥሮ ሃብትና በዱር እንሰሳት ላይ የሚያስከትለውን ችግር በአግባቡ በማጥናት ሊሆን እንደሚገባም ነው ዶክተር መክብብ ያሳሰቡት።

እርሳቸው እንደሚሉት ከሆነ የመንግስት የኢንቨስትመንት ፖሊሲ ትግበራ በተለይም በመሬት አጠቃቀም ረገድ የዱር እንሰሳትን ያማከለ አይደለም። 

በዱር እንስሳቱ ላይ በተለያዩ ህገ-ወጥ መንገዶች ለተለያዩ ዓላማዎች ተብሎ የሚፈፀመው አደንና እንስሳቱን በድብቅ የማሸሽ ተግባርም ዘርፉ ላይ ያንዣበበ አደጋ መሆኑም ተጠቁሟል። 

"አንድ ዝሆን የገደለ ሰው የሚተላለፍበት ቅጣት 30 ሺህ ብር ወይም የ5 አመት እስራት ነው፤ ሆኖም ግን አንድ የዝሆን ጥርስ በህገ ወጥ መንገድ ለገበያ የሚቀርበው በ30 እና በ40 ሺህ ዶላር ነው" የሚሉት ዶክተር መክብብ እንስሳቱን ለመጠበቅና ለማልማት ታስቦ የወጣው ህግ ክፍተቶች ያሉበት መሆኑን አንደሚያሳይ ገልፀዋል።

ዘርፉን የሚወክለው ተቋም አሰራር ደካማ መሆን፣ የቅንጅት ማነስ፣ በጥበቃ ቦታዎች የሚኖረውን  ማህበረሰብ በተጠቃሚነትና በጥበቃው ዙሪያ በበቂ ሁኔታ አለማሳተፍ ሌሎቹ የችግሩ ምንጮች ተብለው ቀርበዋል።

የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ የስራ አስፈጻሚ ዳይሬክተር ዶክተር ማስረሻ ፈጠነ በበኩላቸው፣ በተቋሙ ከዚህ በፊት  በዱር እንሰሳት ላይ ጥናቶችን ያደረገ መሆኑን ገልጸው የሚስተዋሉት ችግሮች ትኩረት ይሻሉ ብለዋል።

በህጉ ላይ የሚስተዋለውን ክፍተትና አጠቃላይ የመሬት አጠቃቀምን ጨምሮ በዘርፉ የሚስተዋሉትን ችግሮች ለመቀነስ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን ጥናቶች ይካሄዳሉ፤ በጥናቶቹ መሰረትም መንግስት የማስተካከያ የፖሊሲ እርምጃ እንዲወስድ ይደረጋል ብለዋል። 

በዱር አንሰሳት ሀብት ልማትና ጥበቃ ዙሪያ የሚሰሩና ከተለያዩ ክልሎች ተወክለው የመጡ ተወያዮችም በቀረቡት ችግሮች ላይ አስተያየታቸውን የሰጡ ሲሆን በዱር እንሰሳት ኃብት ላይ የሚስተዋሉትን ፈተናዎች ለማስወገድ መንግስት ለዘርፉ ትኩረት ሰጥቶ ሊሰራ ይገባዋል ብለዋል።

ዘርፉ ያለውን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጥቅም ግምት ውስጥ በማስገባት ለዘርፉ ትኩረት ሊሰጥ እንደሚገባም አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም