በህገወጥ መንገድ ወደ አገር ውስጥ የገባ ከ1ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያለው ምግብና መድኃኒት ተያዘ - ኢዜአ አማርኛ
በህገወጥ መንገድ ወደ አገር ውስጥ የገባ ከ1ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያለው ምግብና መድኃኒት ተያዘ
መቀሌ ጥር 16/2011 በህገ ወጥ መንገድ ወደ አገር ውስጥ የገባ ከ1 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያለው ምግብና መድኃኒት መያዛቸውን በኢትዮጵያ የምግብ፣የመድኃኒትና ጤና እንክብካቤ አስተዳደርና ቁጥጥር ባለሥልጣን አስታወቀ።
ባለሥልጣኑ ከትግራይ ክልል ጤና ጥበቃ ቢሮ ጋር በመተባበር ህገወጥ የመድኃኒት ሽያጭ በሚያከናውኑ የመድኃኒት መደብሮች ላይ እርምጃ መወሰዱንም ገልጿል።
የባለሥልጣኑ የሰሜን ኢትዮጵያ ቅርንጫፍ ቢሮ ኃላፊ አቶ ክንፈ ኃይሌ ለኢትዮዽያ ዜና አገልግሎት እንደተናገሩት ምግብና መድኃኒቱ በክልሉ ምዕራባዊ ዞን በኩል ወደ አገር ውስጥ ሲገቡ የተያዙት ባለፉት ስድስት ወራት በተደረገው ክትትል ነው።
ከተያዙ መድኃኒትና ምግብ ውስጥ አሞክሳሲሊን፣ኮስመዲካ፣ደንታሞክስ፣የህፃናት ወተት፣ፈሳሽና ደረቅ ምግብ ይገኙባቸዋል።
በክልሉ በ393 የመድኃኒት መሸጫ ቤቶች በተደረገው ፍተሻ 46ቱ ሕገ ወጥ ድርጊት ሲያከናወኑ መገኘታቸውን አቶ ክንፈ ገልጸዋል።
የመድኃኒት መደብሮቹ አገር ውስጥ እንዲገባ ያልተፈቀደና የመጠቀሚያ ጊዜ ያለፈባቸው መድኃኒት ይዘው መገኘታቸውን አስረድተዋል።
በድርጊቱ ተሳትፎ የነበራቸው 16 የመድኃኒት መደብሮች እስከ ሶስት ወር እንዲዘጉ የተደረገ ሲሆን፣ ለ14 የመድኃኒት መደብሮች ደግሞ ከባድ የጽሑፍ ማስጠንቀቂያ መሰጠቱን ተናግረዋል።
ሌሎች 15 የመድኃኒት መደብሮች ህጋዊ ሰነድ እንዲያቀርቡ ትእዛዝ ተሰጥቷቸው ጉዳያቸው በመጣራት ላይ እንደሚገኝ አመልክተዋል።
የኤች አይ ቪ እና የቲቪ መድኃኒት ፈቃድ ባልተሰጣቸው የግል መድኃኒት ቤቶች መገኘታቸውን በትግራይ ክልል ጤና ጥበቃ ቢሮ የምግብ፣ መድኃኒትና ጤና እንክብካቤ ቁጥጥር ዋና የሥራ ሂደት ባለቤት አቶ ባህረ ተካ አስታውቀዋል።
በሽራሮ ከተማ አንድ የመድኃኒት መሸጫ ቤት አገር ውስጥ ለመግባት ያልተፈቀደ ‘’ቪጎ’’ የተባለ መድኃኒትና ለግል መድኃኒት ቤቶች ያልተፈቀደ መድኃኒት ይዞ በመገኘቱ እንዲዘጋ ተደርጓል ብለዋል፡፡
በዓይደር ሪፈራል ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የመድኃኒት ቤት አስተባባሪ አቶ ሙሌ አብርሃ ታካሚዎች በህገወጥ መንገድ የገባ መድኃኒት የመለየት እድላቸው አነስተኛ በመሆኑ መድኃኒት በሚገዙበት ወቅት ህጋዊ ተቋም መሆኑን ሊያረጋግጡ እንደሚገባ ጠቁመዋል።
የመድኃኒት አቅርቦት አነስተኛ በመሆኑ ታካሚዎች ለህገወጥ መድኃኒት ግዢ እንደሚዳረጉ የገለጹት አስተባባሪው፣ለመደኃኒት አቅርቦት ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ ፋርማሲ ማህበር መቀሌ ቅርንጫፍ አስተባባሪና በዓይደር ሪፈራል ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል መምህር አቶ ብርሃነ ዮሐንስ በበኩላቸው በህገወጥ የመድሃኒት ሽያጭ ላይ ትኩረት ተሰጥቶ አለመሰራቱን አብራርተዋል።
ህገ ወጥ የመድኃኒት ሽያጭ በኅብረተሰቡ ላይ ጉዳት ስለሚያስከትል ማህበሩ ከባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር የመከላከል ሥራ እንደሚያከናውን አስታውቀዋል።
በትግራይ ክልል 503 የመንግሥትና የግል የመድኃኒት ቤቶች መኖራቸውን ከቢሮው የተገኘ መረጃ ያመላክታል።