ዩኒቨርሲቲው የወሎና የአፋርን ሕዝቦች ታሪካዊ ትስስር ለወጣቱ ትውልድ በማስገንዘብ ድርሻውን ይወጣል - ኢዜአ አማርኛ
ዩኒቨርሲቲው የወሎና የአፋርን ሕዝቦች ታሪካዊ ትስስር ለወጣቱ ትውልድ በማስገንዘብ ድርሻውን ይወጣል

ደሴ ጥር 16/2011 የወሎና የአፋርን ሕዝቦች ለዘመናት የዘለቀ ታሪካዊ ትስስር ለወጣቱ ትውልድ በማስገንዘብ ድርሻውን እንደሚወጣ የወሎ ዩኒቨርሲቲ አስታወቀ።
የሁለቱን ሕዝቦች ታሪክ፣ አንድነትና አብሮነት ላይ ያተኮረ ስብሰባ በደሴ ከተማ ተካሂዷል።
የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶክተር አባተ ጌታሁን በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት ዩኒቨርሲቲው የሕዝቦቹን ታሪክ ለትውልዱ ለማስተዋወቅ፣አንድነት ለማጠናከርና ሰላምን በመስበክ ትኩረት ሰጥቶ ይሰራል።
ሕዝቦቹ በባህልና በታሪክ እሴቶቻቸው የማይለያዩ፤ በአንድነትና በመቻቻል በጋራ ሰላማቸውን አስቀጥለው የኖሩ ወንድማማች ሕዝቦች መሆናቸውን ያወሱት ፕሬዚዳንቱ፣የፖለቲካ ጥቅመኞች አንድነታቸው እንዳይጠናከርና ሰላማቸው እንዳይረጋገጥ በማህበራዊ መገናኛ ብዙኃን ሲጥሩ ይስተዋላል ብለዋል።
እውነታውን በጥናት በተደገፈ የኪነ ጥበብ ሥራዎች በመታገዝ ለኅብረተሰቡ ባህላቸውን፣ ታሪካቸውን፣ አንድነታቸውንና አብሮነታቸውን ለማስቀጠል እንደሚሰራ አስታውቀዋል፡፡
ዩኒቨርሲቲው በከፈተው የቴአትርና ጥበባት ትምህርት ክፍል በሕዝቦቹ ላይ የሚያተኩሩ የኪነጥበብ ሥራዎች ለሕዝብ እያደረሱ መሆናቸውንም ገልጸዋል፡፡
የአፋር ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ የባህል ሀብቶች ዳይሬክተር አቶ ሐቢብ መሐመድ በበኩላቸው ክልሉ የሕዝቦቹን ታሪክና ባህል በማስከበርና ለኅብረተሰቡ ሰላም መጠበቅ ሲሰራ መቆየቱን ተናግረዋል።
በተዋሳኝ አካባቢዎች የሕዝቦችን አንድነትና ሰላምን ለማሻከር አሉባልታቸውን የሚነዙ ወገኖች ቢኖሩም፤ ኅብረተሰቡ በየጊዜው በሚያደርገው ውይይት ተቀባይነት እንደሌላቸው ማሳየቱን አስረድተዋል፡፡
ወጣቶች በተሳሳተ መረጃ መነዳት ሳይሆን በእያንዳንዱ ጉዳይ ላይ ምክንያታዊ በመሆን ሰላምን ማስጠበቅና ኢትዮጵያዊ ባህልን ማስቀጠል ይኖርባቸዋል ብለዋል፡፡
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሕግ መምህር ፕሮፌሰር መሐመድ ሐቢቢ እንዳመለከቱት የሕዝቦቹን ታሪክና ማንነት በመገናኛ ብዙኃንና በኪነጥበብ ሥራዎች በማስተዋወቅ ታሪክን ማስቀጠል ያስፈልጋል፡፡
ሰላምና አንድነት ማውራት ብቻ ሳይሆን፤ በተግባር መተርጎም ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።
አርቲስት ደሳለኝ ኃይሉ በበኩሉ የኢትዮጵያን የጥንት ታሪክ በኪነ ጥበብ ሥራዎች ለማንጸባረቅ ብሎም ለውጡን ለማስቀጠል ድርሻችንን እንወጣለን ብሏል፡፡
ሰላምና አንድነትን የሚሰብኩ ሥራዎችን በአገሪቱ የተለያዩ ክፍሎች ለማቅረብ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን አስታውቀዋል።
በስብሰባው አንድነትና ሰላም የሚሰብክ "የሰላም ህይወት በቦርከና ወንዝ ዳርቻዎች" የሚል ቴአትር ቀርቧል።
ቴአትሩ በወሎ፣በአፋርና በኦሮሞ ብሄረሰብ ዞን ከተሞች እንደሚቀርብም ተገልጿል፡፡
በስብሰባው ከዩኒቨርሲቲው፣ከወሎ፣ከኦሮሞ ብሄረሰብ አስተዳደር ዞንና ከአፋር ክልል የተውጣጡ ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።