ዓለም አቀፍ የቀይ መስቀል ኮሚቴ ለኢትዮጵያ የሚሰጠውን ድጋፍ አጠናክሮ ይቀጥላል ተባለ

57

አዲስ አበባ ጥር 16/2011 የውጭ ጉዳይ ሚስትር ክቡር ዶ/ር ወርቅነህ ገበየሁ ከዓለም አቀፉ የቀይ መስቀል ኮሚቴ ፕሬዝዳንት ፒተር ማዉረር ጋር በጋራ ጉዳዮች ላይ መከሩ።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩና የኮሚቴው ፕሬዚዳንት ውይይቱን ያካሄዱት በስዊዘርላንድ ዳቮስ እየተካሄደ ካለው ዓለም አቀፍ የኢኮኖሚክ ፎረም ጎን ለጎን ነው።

በውይይቱ ላይም ዶክተር ወርቅነህ ዓለም አቀፉ የቀይ መስቀል ኮሚቴ በኢትዮጵያ እያደረገ ያለውን ድጋፍ አድነቀው ይህንኑ አጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።

በኢትዮጵያ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የተጀመረውን ሁሉን አቀፍ ለውጥ በተመለከተም ለፕሬዚዳንቱ ገለጻ ማድረጋቸውን የውጭ ጉዳይ ቃል አቀባይ ፅህፈት ቤት ለኢዜአ በላከው መግለጫ አመልክቷል። 

በኢትዮጵያ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በፖለቲካ፣ በማህበራዊ እና በኢኮኖሚ ዘርፎች በታየው ለውጥ ምክንያት የተስፋ ንፋስ እየነፈሰ ነው ሲሉም ሚኒስትሩ ተናግረዋል።

ዓለም አቀፍ የቀይ መስቀል ኮሚቴ ፕሬዘድንት ፒተር ማዉረር በበኩላቸው በኢትዮጵያ እየታየ ያለውን ለውጥ አድንቀዋል።

በክልሉ ቀጠናዊ ውህደት እንዲመስረትና ሰላም እንዲሰፍን ኢትዮጵያ የእተጫወተች ያለውን ሚና በተመለከተም ያለቸውን እድናቆት ገልጸዋል።

ዓለም አቀፍ የቀይ መስቀል ኮሚቴ ለኢትዮጵያ የሚያደርገውን ድጋፍም አጠናክሮ እንደሚቀጥል ቃል ገብተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም