በሊቦ ከምከም ወረዳ የተሽከርካሪ አደጋ የሰዎችን ህይወት አጠፋ

87

ባህርዳር ጥር 16/2011 በደቡብ ጎንደር ዞን ሊቦ ከምከም ወረዳ በደረሰ የተሽከርካሪ አደጋ የሁለት ሰዎች ህይወት  ሲጠፋ  በሰባት  ሰዎች ላይ ደግሞ ከባድ የአካል ጉዳት መድረሱን ፖሊስ አስታወቀ፡፡

በፋሲል የእግር ኳስ ክለብ  ደጋፊዎች ላይ  የደረሰው ይሄው አደጋ  ትናንት ምሽት አንድ ሰዓት አካባቢ  በሊቦ ከምከም ወረዳ ጣራ ገዳም ቀበሌ አርኖ ተብሎ በሚጠራው ቦታ  በመገልበጡ ነው፡፡

የወረዳው  ፖሊስ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ዋና ኢንስፔክተር አምሳሉ ሞነን ለኢዜአ እንደገለጹት  የታርጋ ቁጥሩ ኮድ 3 - 21409 አማ በሆነው  የህዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪ በደረሰው አደጋ ህይወታቸው ከጠፋውና በከባድ ከቆሰሉት ሌላ 34 ሰዎች ቀላል ጉዳት ደርሶባቸዋል፡፡

ቀላል ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች በአዲስ ዘመንና ጎንደር ሆስፒታል የህክምና እርዳታ ተደርጎላቸው ወደ ቤተሰቦቻቸው ተልከዋል።

ከባድ የአካል ጉዳት የደረሰባቸው ደግሞ በጎንደር ሪፈራል ሆስፒታል ህክምና እየተደረገላቸው እንደሚገኝ አመልክተው፤ የሟቾች አስከሬንም ቤተሰቦቻቸው በመረከብ   ዛሬ የቀብር ስነ-ስርዓታቸው  መፈጸሙን  ዋና ኢንስፔክተሩ ተናግረዋል፡፡

የእግር ኳስ ቡድኑ ደጋፊዎች ላይ አደጋው የደረሰው  በባህርዳር ብሄራዊ ስታዲየም ትናንት ከባህር ዳር ከተማ አቻው ጋር የነበረውን ጨዋታ ደግፈው ወደ ጎንደር ሲመለሱ  ነው።

የአደጋው ምክንያት እየተጣራ እንደሚገኝ ያመለከቱት ዋና ኢንስፔክተሩ  አሸከርካሪውን ለጊዜው ማግኘት እንዳልተቻለ ጠቁመዋል።

በተጨማሪው በዚሁ አካባቢ  ሌላ  ደጋፊዎችን አሳፍሮ ይጓዝ የነበረ የታርጋ  ቁጥሩ ኮድ 3- 07751አማ  የሆነ  የህዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪ ተገልብጦ በሰው ህይወት ላይ  ጉዳት ባይደረስም መጠነኛ የንብረት ውድመት ማጋጠሙን ተመልክቷል፡፡

የፋሲል የእግር ኳስ ክለብ  ደጋፊዎች ማህበር ሊቀመንበር  አቶ ጋሻው አስማረ   በደረሰው ድንገተኛ አደጋ ህይወታቸውን በለፈው ደጋፊች  የተሰማቸውን ጥልቅ ሀዘን ገልጸዋል፡፡

የባህር ዳርና የፋሲል እግር ኳስ ክለቦች  ትናንት በነበራቸው ግጥሚያ ዜሮ ለዜሮ ነው የተለያዩት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም