ቀጥታ፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ወርቅነህ በምስራቅ አፍሪካ ቀጠናዊ ትብብር ዙሪያ በዳቮስ ገለፃ አደረጉ

አዲስ አበባ ጥር 16/2011 በአፍሪካ ቀንድ የተጀመረው ትብብርና ውህደት ተቋማዊ ይዘት እንዲኖረው ምክክር እየተደረገና ህጋዊ ማዕቀፎች እየተዘጋጁለት መሆኑን የኢፌዲሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ ገለፁ።

ዶክተር ወርቅነህ በስዊዘርላንድ ዳቮስ በመካሄድ ላይ ባለው የዓለም ኢኮኖሚክ ፎረም በመገኘት በምስራቅ አፍሪካ ቀንድ ቀጠናዊ ትብብር ዙሪያ ገለፃ አድርገዋል፡፡

በንግግራቸውም የአፍሪካ ቀንድ ትብብር አሁን ካለበት ደረጃ እንዲደርስ የቅድሚያ ተነሳሽነቱን በመውሰድ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ጉልህ ሚና እንዳላቸው አንስተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአጭር ጊዜ በአገር ውስጥ ፖለቲካዊ መግባባት እንዲፈጠር፣ ሰላም እንዲሰፍንና የዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታ መሰረት እንዲጣል ማድረጋቸውንም አስንተዋል።

በአፍሪካ ቀንድ አገሮች በጋራ ጥቅም ላይ የተመሰረተ ትብብር እና ውህደት እንዲመሰረት በማድረግ ሂደትም የጠቅላይ ሚኒስትሩ ሚና ከፍተኛ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ለአካባቢው ሰላም መስፈን የኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ የወሰዱትን የበኩላቸውን ፋና ወጊ እርምጃም ዶክተር ወርቅነህ አድንቀዋል።

የአፍሪካ ቀንድ ቀጠና ለዘመናት በእርስ በርስ ብጥብጥ እና በጠላትነት አስተሳሰብ ይመራ እንደነበር አስታውሰው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን የኢትዮጵያ እና የኤርትራ መሪዎች በወሰዱት ብልህ አመራር ቀጠናዊ ትብብርና ውህደት ለመመስረት አስችሏል ብለዋል።

በቀጠናው አሁን የተጀመረው የትብብር መንፈስ የህዝቦችን የጋራ ጥቅም በማከለ መልኩ ዘላቂ እንዲሆን ለማድረግ የድንበር ጉዳይ፣ ህገ ወጥ የሰዎች ዝውውር እና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮችም ውይይት እየተካሄደባቸው መሆኑን በጉባኤው ላይ አብራርተዋል።

በኢትዮጵያ፣ ኤርትራ ፣ ጅቡቲ፣ ሶማሊያ እና ሌሎች ጎረቤት አገሮች ላይ የሚታየው የትብብርና አብሮ የመስራት ፍላጎት ለቀጠናው ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካ ብሎም ለዓለም ሰላም ወሳኝ ሚና እንዳለውም አብራርተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም